Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 5:00

[1] ጌታችን ኢየሱስም ይህን ነገር ከፈጸመ በኋላ ከገሊላ ተነሥቶ ወደ ይሁዳ አውራጃ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ ደረሰ።

[2] ብዙዎች በሽተኟችም ተከተሉት፤ በዚያም ፈወሳቸው።

[3] ፈሪሳውያንም ሊፈትኑት ወደ እርሱ መጥተው ፥ “በማናቸውም በበደለችው ሁሉ ሚስቱን ሊፈታ ለሰው ይገባልን?” አሉት።

[4] እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው ፥ “አላነበባችሁምን? በመጀመሪያ የፈጠራቸው እርሱ ወንድና ሴት አደረጋቸው።”

[5] እንዲህም አለ ፥ “ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ትቶ ሚስቱን ይከተላል፤ ሁለቱም አንድ አካል ይሆናሉ።

[6] እንኪያስ ሁለት አይደሉም፤ አንድ አካል ናቸው እንጂ፤ እግዚአብሔርም አንድ ያደረገውን ሰው አይለይ።”

[7] እነርሱም ፥ “እንኪያ የፍቺዋን ደብዳቤ ሰጥተው እንዲፈቱአት ሙሴ ለምን አዘዘ?” አሉት።

[8] እርሱም አላቸው ፥ “ሙሴስ ስለ ልባችሁ ክፋት ሚስቶቻችሁን እንድትፈቱ ፈቀደላችሁ፤ ቀድሞ ግን እንዲህ አልነበረም።

[9] እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል፤ የተፈታችውንም ያገባ ያመነዝራል።”

[10] ደቀ መዛሙርቱም ፥ “የባልና የሚስት ሥርዐት እንዲህ ከሆነስ መጋባት መልካም አይደለም ” አሉት።

[11] እርሱም አላቸው ፥ “ይህ ለተሰጠው ነው እንጂ ለሁሉ የሚቻል አይደለም።

[12] ከእናታቸው ማኅፀን እንዲሁ የተወለዱ ጃንደረቦች አሉና፤ ሰዎች የሰለቡአቸውም ጃንደረቦች አሉ፤ ስለ መንግሥተ ሰማያትም ራሳቸውን ጃንደረባ ያደረጉ አሉ፤ መታገሥ የሚችል ግን ይታገሥ።”

[13] ከዚህም በኋላ እጁን በላያቸው ጭኖ ይጸልይ ዘንድ ሕፃናትን አመጡለት፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ተቈጡአቸው።

[14] ጌታችን ኢየሱስም ፥ “ሕፃናትን ተዉአቸው፤ ወደ እኔም ይመጡ ዘንድ አትከልክሉአቸው፤ መንግሥተ ሰማያት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና ” አላቸው።

[15] እጁንም በላያቸው ጫነባቸውና ከዚያ ሄደ።

[16] እነሆም አንድ ጐልማሳ መጥቶ ፥ “ቸር መምህር ሆይ የዘለዓለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ከበጎ ሥራ ወገን ምን ላድርግ?” አለው።

[17] እርሱም ፥ “ለምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ እግዚአብሔር በቀር ማንም ቸር የለም፤ ወደ ሕይወት ልትገባ ብትወድድስ ትእዛዛትን ጠብቅ ” አለው።

[18] እርሱም ፥ “የትኟቹን?” አለው፤ ጌታችን ኢየሱሱም አለው፥ “አትግደል፥ አታመንዝር፥ አትስረቅ፥ በሐሰትም አትመስክር፥

[19] አባትህንና እናትህን አክብር፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ።”

[20] ያም ጐልማሳ ፥ “ይህን ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ፤ እንግዲህ የቀረኝ ምንድን ነው?” አለው።

[21] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለው ፥ “ፍጹም ልትሆን ብትወድስ፥ ሂድና ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለድኾች ስጥ፤ ሰማያዊ ሀብትንም ታገኛለህ፤ መጥተህም ተከተለኝ።”

[22] ጐልማሳውም ይህን ነገር ሰምቶ ሀብቱ ብዙ ነበርና እያዘነ ሄደ።

[23] ጌታችን ኢየሱስም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው ፥ “እውነት እላችኋለሁ፤ ባለጸጋ ወደ መንግሥተ ሰማያት ይገባ ዘንድ ጭንቅ ነው።

[24] ዳግመኛም እላችኋለሁ ፥ ባለጸጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል።”

[25] ደቀ መዛሙርቱም ይህን በሰሙ ጊዜ ፥ “እንግዲያ ማን ሊድን ይችላል?” እያሉ እጅግ ተደነቁ።

[26] ጌታችን ኢየሱስም አያቸውና ፥ “በሰው ዘንድ ይህ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል ” አላቸው።

[27] ከዚህም በኋላ ጴጥሮስ መልሶ ፥ “እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ እንግዲህ ምን እናገኛለን?” አለው።

[28] ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው ፥ “እውነት እላችኋለሁ፤ የተከተላችሁኝ እናንተ በዳግም ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በተቀመጠ ጊዜ እናንተም በዐሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ፤ በዐሥራ ሁለቱም ነገደ እሥራኤል ትፈርዳላችሁ።

[29] ስለ ስሜም ቤትን፥ ወይም ወንድሞችን፥ ወይም እኅቶችን፥ ወይም አባትን፥ ወይም እናትን፥ ወይም ሚስትን፥ ወይም ልጆችን፥ ወይም ርስትን የተወ ሁሉ መቶ ዕጥፍ ዋጋ ያገኛል፤ የዘለዓለም ሕይወትንም ይወርሳል።

[30] ነገር ግን ብዙዎች ፊተኟች ኋለኟች ይሆናሉ፤ ኋለኟችም ፊተኟች ይሆናሉ።

የማቴዎስ ወንጌል። — Chapters