Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 2:44

[1] ለቅዱሳን ስለሚደረገው አገልግሎት የምጽፍላችሁ ብዙ አለኝ

[2] እናንተ እንደምትተጉ አውቃለሁና፤ ስለዚህም “የአካይያ ሰዎች እኮ ከአምና ጀምሮ አዘጋጅተዋል ” ብዬ በመቄዶንያ ሰዎች ዘንድ አመሰገንኋችሁ፤ እነሆም የእናንተ መፎካከር ብዙዎችን ሰዎች አትግቶአቸዋል።

[3] በዚህም ያመሰገንናችሁ ምስጋና በእነርሱ ዘንድ ሐሰት እንዳይሆንብን፥ እንደ ነገርናቸውም ተዘጋጅታችሁ እንዲያገኙአችሁ ወንድሞችን ወደ እናንተ ላክናቸው።

[4] ምናልባት የመቄዶንያ ሰዎች ከእኔ ጋር ቢመጡና ሳታዘጋጁ ቢያገኙአችሁ እናንተ ታፍራላችሁ ባልልም እኛ ስለ እናንተ ከነገርናቸው የተነሣ እናፍራለን።

[5] ስለዚህም አስቀድመው ወደ እናንተ መጥተው በቅድሚያ የተናገራችኋትን በረከታችሁን እንዲያዘጋጁ ወንድሞችን ማለድሁ፤ እንደዚህም የተዘጋጀ ይሁን፤ በረከትን እንደምታገኙበት እንጂ በንጥቂያ እንደ ተወሰደባችሁ አይሁን።

[6] አሳንሶ የሚዘራ ለእርሱ እንዲሁ መከሩ ያንስበታል፤ በብዙ የሚዘራ ግን በብዙ ያመርታል።

[7] ሁሉ ልቡ እንደ ወደደ ያድርግ፤ በደስታ ይስጡ እንጂ በግድ አይሆንም፤ እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና።

[8] እግዚአብሔር መልካሙን ነገር ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል፤ ፍጹም በረከቱንም ለዘወትር ያበዛላችሁ ዘንድ፥ ለሁሉም ታተርፉታላችሁ፤ በጎ ሥራ መሥራትንም ታበዛላችሁ።

[9] “በተነ፤ ለድሃም ሰጠ፤ ጽድቁም ለዘለዓለም ይኖራል ” ብሎ መጽሐፍ እንደ ተናገረ።

[10] እርሱ ዘርን ለዘሪ ይሰጣል፤ እህልንም ለምግብ ይሰጣችኋል፤ ዘራችሁንም ያበዛላችኋል፤ የጽድቃችሁንም መከር ያበጃል።

[11] ለብዙ ሰዎች ስለ ሰጣችሁም የእግዚአብሔርን ምስጋና በምታደርግላችሁ ልግስና ሁሉ ባለጸጎች ትሆናላችሁ።

[12] ይህቺ የዚህ ሥራ አገልግሎት ግዳጅ የምትፈጽመው ለዚህ ለቅዱሳን ችግር መሟላት ብቻ አይደለም፤ በቅዱሳን ዘንድም ደግሞ የእግዚአብሔርን ምስጋና ታበዛለች።

[13] ክርስቶስ ላስተማራት ትምህርት ታዝዛችኋልና፥ ሁላችሁም ደስ ብሎአችሁና ተባብራችሁ አወጣጥታችኋልና በዚች በሃይማኖታችሁ ፈተና ምክንያት እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤

[14] እነርሱም ስለ እናንተ ይጸልያሉ፤ ስለ አደረባችሁ ታላቅ የእግዚአብሔር ጸጋም ሊያዩአችሁ ይመኛሉ።

[15] ስለማትመረመርና ባላሰቡአት ጊዜ ስለምትመጣው ጸጋው እግዚአብሔር ይመስገን።

ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2 — Chapters