[1] ስለዚህ እንደ ቸርነቱ የሰጠን ይህ መልእክት አለንና አንሰለችም።
[2] ነገር ግን በስውር የሚሠራውን አሳፋሪ ሥራ እንተወው፤ በተንኰልም አንመላለስ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅል፤ ለሰውም ሁሉ አርአያ ስለ መሆን እውነትን ገልጠን በእግዚአብሔር ፊት ራሳችንን እናጽና።
[3] ወንጌላችን የተሰወረ ቢሆንም እንኳ፥ የተሰወረባቸው ለሚጠፉት ነው።
[4] እግዚአብሔርን የሚመስለው የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው የዚህ ዓለም አምላክ ልባቸውን አሳውሮአልና።
[5] ኢየሱስ ክርስቶስን ጌታ እንደ ሆነ እንሰብካለን እንጂ ራሳችንን የምንሰብክ አይደለም፤ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስም ብለን ራሳችንን ለእናንተ አስገዛን።
[6] በጨለማ ውስጥ “ብርሃን ይብራ ” ያለ እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት የክብሩን ዕውቀት ብርሃን በልባችን አብርቶልናልና።
[7] ነገር ግን ከእኛ ያይደለ ከእግዚአብሔር የተገኘ ታላቅ ኀይል ይሆን ዘንድ በሸክላ ዕቃ ውስጥ ይህ መዝገብ አለን።
[8] በሁሉ መከራን እንቀበላለን፤ ነገር ግን አንጨነቅም፤ እንናቃለን፥ ነገር ግን ተስፋ አንቈርጥም።
[9] እንሰደዳለን፤ ነገር ግን አንጣልም፤ እንወድቃለን፤ ነገር ግን አንጠፋም።
[10] የክርስቶስ ሕይወቱ በዚህ በሟች ሰውነታችን ላይ ይገለጥ ዘንድ፥ ዘወትር የክርስቶስን ሞት በሥጋችን እንሸከማለን።
[11] በሕይወት የምንኖር እኛም በሟች ሰውነታችን ላይ የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቱ ይገለጥ ዘንድ፥ ዘወትር ስለ ኢየሱስ ክስርቶስ ብለን ተላልፈን ለሞት እንሰጣለን።
[12] ስለዚህም ሞት በእኛ ላይ፥ ሕይወትም በእናንተ ላይ ይሠራል።
[13] አንድ የእምነት መንፈስ አለን፤ መጽሐፍ ፥ “አመንሁ፤ ስለዚህም ተናገርሁ” እንዳለ እኛም አመን፤ ስለዚህም ተናገርን።
[14] ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ያስነሣው እርሱ እኛንም እንደ እርሱ እንዲያስነሣን፥ ከእናንተም ጋር በፊቱ እንዲያቆመን እናውቃለን።
[15] ጸጋው በብዙዎች ላይ ትትረፈረፍ ዘንድ፥ የእግዚአብሔርም የክብሩ ምስጋና ይበዛ ዘንድ ሁሉ ስለ እናንተ ነውና።
[16] ስለዚህ አንሰልች፤ በውጭ ያለው ሰውነታችን ያረጃልና፤ በውስጥ ያለው ሰውነታችን ግን ዘወትር ይታደሳል።
[17] ቀላል የሆነው የጊዜው መከራችን ክብርንና ጌትነትን ለዘለዓለም አብዝቶ ያደርግልናልና።
[18] የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ተስፋ አናደርግም፤ የሚታየው ኀላፊ ነውና፥ የማይታየው ግን ለዘለዓለም የሚኖር ነው።