Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 2:27

[1] እንግዲህ እያዘንሁ ወደ እናንተ እንዳልመጣ በልቤ ይህን ወሰንሁ።

[2] እኔ ካሳዘንኋችሁማ እኔ ካሳዘንሁት በቀር ማን ደስ ያሰኘኛል?

[3] የእኔ ደስታ የሁላችሁ እንደ ሆነ በሁላችሁ አምኛለሁና በመጣሁ ጊዜ ደስ ሊያሰኙኝ ከሚገባቸው ኀዘን እንዳያገኘኝ ይህን ጻፍሁላችሁ።

[4] ከብዙ መከራና ከልብ ጭንቀት የተነሣ በብዙ እንባ ይህን ጽፌላችኋለሁ፤ ነገር ግን እጅግ እንደምወዳችሁ እንድታውቁ ነው እንጂ እንድታዝኑ አይደለም።

[5] ማንም ያሳዘነኝ ቢሆን፥ እኔን ብቻ ያሳዘነ አይደለም። ከእናንተ አንድ ሳይቀር ሁላችሁንም አሳዘነ እንጂ፤ አሁንም ሥርዐት አላጸናባችሁም።

[6] እንደዚህ ላለው ሰው ከእናንተ ከብዙዎች ያገኘችው ይህች ተግሣጽ ትበቃዋለች።

[7] ደግሞም እንዲህ ያለው ሰው ከኀዘን ብዛት የተነሣ እንዳይዋጥ ይቅር ልትሉትና ልታጽናኑት ይገባል።

[8] ስለዚህም ከእርሱ ጋር ፍቅርን እንድታጸኑ እማልዳችኋለሁ።

[9] ስለዚህም በሁሉ ትታዘዙኝ እንደ ሆነ፥ ፈቃዳችሁን ዐውቅ ዘንድ ጻፍሁላችሁ።

[10] ይቅር የምትሉት ቢኖር፥ እኔም ከእናንተ ጋር ይቅር እለዋለሁ፤ እኔም ይቅር ያልሁትን በክርስቶስ ፊት ስለ እናንተ ይቅር ብያለሁ።

[11] ሰይጣን እንዳያታልለን አሳቡን የምንስተው አይደለምና።

[12] ለክርስቶስም ወንጌል ጢሮአዳ በደረስሁ ጊዜ በእግዚአብሔር በሩ ተከፈተልኝ።

[13] ወንድሜን ቲቶን ስላላገኘሁት ለሰውነቴ ዕረፍት አላገኘሁም፤ ነገር ግን ከእርሱ ተለይቼ ወደ መቄዶንያ ሄድሁ።

[14] በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር ድል በመንሣቱ የሚጠብቀን፥ በየሀገሩም ሁሉ የዕውቀቱን መዓዛ በእኛ የሚገልጥ እግዚአብሔር ይመስገን።

[15] በሚድኑትና በሚጠፉት ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ እኛ ነንና።

[16] የሞት መዓዛ የሚገባቸው ለሞት፥ የሕይወት መዓዛ የሚገባቸውም ለሕይወት ናቸው፤ ነገር ግን ይህ የሚገባው ማነው?

[17] የእግዚአብሔርን ቃል በሌላ ቀላቅለው እንደሚሸቅጡ እንደ ብዙዎች አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላከ በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ እንናገራለን።

ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2 — Chapters