[1] ወንድሞች ሆይ፥ ለመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ጸጋ እነግራችኋለሁ።
[2] በብዙ መከራ ከመፈተናቸው የተነሣ ደስታቸው በዝቶአልና፤ በድህነታቸው ጥልቅነትም የለጋስነታቸው ባለጠግነት በዝታለችና።
[3] እነርሱ ሲቻላቸው፥ ሳይቻላቸውም እንስጥ በማለት ቈራጦች ለመሆናቸው ምስክራቸው እኔ ነኝና።
[4] ለቅዱሳን ስለሚሆነው አገልግሎት እንዲተባበሩ ይህን ቸርነት መላልሰው ማለዱን።
[5] እነርሱ አስቀድመው በፈቃዳቸው፥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሰውነታቸውን ለእግዚአብሔርም፥ ለእኛም አሳልፈው ሰጥተዋልና እኛ እንደ አሰብነው አይደለም፤
[6] ይህንም የቸርነት ሥራ እንደ ጀመረ ይፈጽምላችሁ ዘንድ ቲቶን ማለድነው።
[7] በሁሉ ነገር በእምነትና በቃል፥ በዕውቀትም፥ በትጋትም በእናንተ ዘንድ በሆነው ሁሉ እኛን በመውደዳችሁ ፍጹማን እንደ ሆናችሁ፥ እንዲሁም ደግሞ ይህቺን ስጦታ አብዙ።
[8] በግድ የምላችሁ አይደለም፤ ነገር ግን ከእናንተ ለዚህ ሥራ የሚተጉለት አሉና የፍቅራችሁን እውነተኛነት አሁን መርምሬ ተረዳሁ።
[9] የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸርነቱን ታውቃላችሁ፤ በእርሱ ድህነት እናንተ ባለጸጎች ትሆኑ ዘንድ እርሱ ባለጸጋ ሲሆን፥ ስለ እናንተ ራሱን ድሃ አደረገ።
[10] በዚህም የሚጠቅማችሁን እመክራችኋለሁ፤ ይህን ከማድረጋችሁ በፊት ፈቅዳችኋልና፤ ከአምና ጀምሮም ይህን ጀምራችኋል።
[11] አሁንም አድርጉ፤ ፈጽሙም፤ መፍቀድ ከመሻት ነውና፤ ማድረግም ከማግኘት ነውና።
[12] ፈቃድ ካለም፥ ሰው በሚቻለው መጠን ቢሰጥ ይመሰገናል፤ በማይቻለውም መጠን አይደለም።
[13] በዚህ ወራት ተካክላችሁ እንድትኖሩ ነው እንጂ ሌላው እንዲያርፍ እናንተን የምናስጨንቅ አይደለም።
[14] ኑሮአችሁ በሁሉ የተካከለ ይሆን ዘንድ፥ የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጕuድለት ይመላልና፥ የእነርሱም ትርፍ የእናንተን ጕuድለት ይመላልና።
[15] መጽሐፍ እንዳለ ፥ “ብዙ ያለው አላተረፈም፤ ጥቂት ያለውም አላጐደለም።”
[16] በቲቶ ልብ ስለ እናንተ ያን መትጋት የሰጠ እግዚአብሔር የተመሰገነ ነው።
[17] ልመናችንንም ተቀብሎ፥ ጨክኖ ወደ እናንተ ይመጣ ዘንድ ቸኵuሏል።
[18] ስለ ወንጌል ትምህርት አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ያመሰገኑትን ወንድማችንንም ከእርሱ ጋር ልከናል።
[19] ይህም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ክብርና የእኛን በጎ ፈቃድ ለማሳየት በምናገለግልባት በዚች ጸጋ ከእኛ ጋር አንድ ይሆን ዘንድ በአብያተ ክርስቲያናት ተሾመ።
[20] ስለምናገለግለው ስለዚህ ለጋስ ስጦታ ማንም እንዳይነቅፈን እንጠነቀቃለን።
[21] በእግዚአብሔር ፊት ብቻ ያይደለ፥ ነገር ግን በሰው ፊትም መልካሙን ነገር እናስባለንና።
[22] በብዙ የፈተንነውንና በሁሉም ነገር ትጉህ ሆኖ ያገኘነውን አሁንም በእናንተ እጅግ ስለሚታመን ከፊት ይልቅ እጅግ ትጉ የሚሆነውን ወንድማችንን ከእነርሱ ጋር እንልካለን።
[23] ቲቶም ቢሆን፥ ስለ እናንተ አብሮኝ የሚሠራ ጓደኛዬ ነው፥ ወንድሞቻችንም ቢሆኑ፥ ለእግዚአብሔር ክብር የአብያተ ክርስቲያናት ሐዋርያት ናቸው።
[24] አሁንም መዋደዳችሁንና እኛም በእናንተ የምንመካበትን ሥራ በአብያተ ክርስቲያናት ፊት በግልጥ አሳዩአቸው።