Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 5:22

[1] በስንፍናዬ እናገር ዘንድ ጥቂት ልትታገሡኝ ይገባ ነበር፤ ቢሆንም በርግጥ ታገሡኝ፤

[2] ለእግዚአብሔር የሚገባ ቅንዐት እቀናላችኋለሁና፤ ወደ እርሱ አቀርባችሁ ዘንድ ለአንዱ ንጹሕ ድንግል ሙሽራ ለክርስቶስ አጭቻችኋለሁና።

[3] ነገር ግን እባብ ሔዋንን በተንኰሉ እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ከክርስቶስ የዋህነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ።

[4] ወደ እናንተ የመጣና እኛ ወደ አላስተማርናችሁ ወደ ሌላ ኢየሱስ የጠራችሁ ቢኖር፥ ወይም ያልተቀበላችሁት ሌላ መንፈስ ቢኖር፥ ወይም ያልተማራችሁት ሌላ ወንጌል ቢኖር ልትጠብቁን ይገባል።

[5] እኔ ግን ሌሎች ሐዋርያት ከአስተማሩት ያጐደልሁባችሁ የለም ይመስለኛል።

[6] እኔ በአነጋገሬ አላዋቂ ብሆንም በዕውቀት ግን እንዲሁ አይደለሁም፤ ነገር ግን ሁሉን በሁሉ እገልጥላችኋለሁ።

[7] ወይስ ራሴን በሁሉ ያዋረድሁ በደልሁ ይሆን? እናንተ ከፍ ከፍ ትሉ ዘንድ፥ የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ዋጋ አስተምሬአችኋለሁና።

[8] እናንተን አገለግል ዘንድ፥ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ተቀብዬ፥ ለምግቤ ያህል ወሰድሁ፤

[9] ከእናንተ ዘንድ በነበርሁበት ጊዜም፥ ስቸገር ገንዘባችሁን አልተመኘሁም። ባልበቃኝም ጊዜ ወንድሞቻችን ከመቄዶንያ መጥተው አሙአሉልኝ፤ በእናንተም ላይ እንዳልከብድባችሁ በሁሉ ተጠነቀቅሁ፤ ወደ ፊትም እጠነቀቃለሁ።

[10] የክርስቶስ ዕውነት አብሮኝ ይኖራልና፥ ይህቺ ደስታዬ በአካይያ አውራጃ አልተከለከለችብኝም።

[11] ስለምን ነው? አልወዳችሁምና ነውን? እንደምወድዳችሁስ እግዚአብሔር ያውቃል።

[12] ነገር ግን ያደረግሁትም ቢሆን፥ የማደርገውም ቢሆን፥ እነርሱ እንደ እኛ የሚመኩበትን ያገኙ ዘንድ፥ ምክንያት የሚሹትን ምክንያት አሳጣቸው ዘንድ ነው።

[13] የሚተነኰሉ፥ ራሳቸውን የክርስቶስን ሐዋርያት የሚያስመስሉ፥ ዐመፅንም የሚያደርጉ ሐሰተኟች ሐዋርያት አሉና።

[14] ይህም አያስደንቅም፤ ሰይጣን ራሱ ተለውጦ እንደ ብርሃን መልአክ ይመስላልና።

[15] መልእክተኟቹም የጽድቅ መላእክትን ቢመስሉ፥ ይህ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜያቸው ግን እንደ ሥራቸው ነው።

[16] ደግሞም እንዲህ እላለሁ ፥ ሰነፍ የሚያደርገኝ አይኑር፤ ያውም ብሆን እኔ ጥቂት እመካ ዘንድ እንደ ሰነፍ እንኳ ብሆን ተቀበሉኝ።

[17] ይህም ቢሆን የምናገረው ለእግዚአብሔር የሚገባ አይደለም፤ ነገር ግን ስለዚህች ትምክሕቴ እንደ ሰነፍ እናገራለሁ።

[18] በሥጋዊ ሥርዐት የሚመኩ ብዙዎች ናቸውና እኔ ደግሞ እመካለሁ።

[19] እናንተ ልባሞች ስትሆኑ ሰነፎችን መስማት ደስ ያሰኛችኋልና።

[20] የሚገዙአችሁንና የሚቀሙአችሁን፥ መባያ የሚያደርጓችሁንና የሚታበዩባችሁን፥ ፊታችሁንም በጥፊ የሚመትWaችሁን ትታገሡአቸዋላችሁና።

[21] እኛ እንደ ደካሞች መስለን እንደ ነበርን፥ ይህን በውርደት እናገራለሁ፤ ነገር ግን ማንም በሚደፍርበት እኔ ደግሞ እደፍራለሁ።

[22] እነርሱ ዕብራውያን ቢሆኑ እኔም እንደ እነርሱ ነኝ፤ እነርሱ እስራኤላውያን ቢሆኑ እኔም እንደ እነርሱ ነኝ፤ እነርሱ የአብርሃም ልጆች ቢሆኑ እኔም እንደ እነርሱ ነኝ።

[23] እነርሱ የክርስቶስ አገልጋዮች ቢሆኑም እኔም እንደ ሰነፍ ለራሴ እናገራለሁ፤ እኔ እበልጣለሁ፤ እጅግም ደከምሁ፤ ብዙ ጊዜ ተገረፍሁ፤ ብዙ ጊዜም ታሰርሁ፤ ብዙ ጊዜም ለሞት ተዘጋጀሁ።

[24] አይሁድ አንዲት ስትቀር አምስት ጊዜ አርባ አርባ ገረፉኝ።

[25] ሦስት ጊዜ በበትር ደበደቡኝ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ መቱኝ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረች፤ በጥልቁ ባሕር ውስጥ ስዋኝ አድሬ፥ ስዋኝ ዋልሁ።

[26] በመንገድ ዘወትር መከራ እቀበል ነበር፤ በወንዝም መከራ ተቀበልሁ፤ ወንበዴዎችም አሠቃዩኝ፤ ዘመዶቼም አስጨነቁኝ፤ አሕዛብ መከራ አጸኑብኝ፤ በከተማ መከራ ተቀበልሁ፤ በበረሃም መከራ ተቀበልሁ፤ በባሕርም መከራ ተቀበልሁ፤ ሐሰተኟች መምህራን መከራ አጸኑብኝ።

[27] በድካምና በጥረት፥ ብዙ ጊዜም ዕንቅልፍ በማጣት፥ በመራብና በመጠማት፥ አብዝቶም በመጿም፥ በብርድና በመራቆት ተቸገርሁ።

[28] የቀረውንም ነገር ሳልቈጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው።

[29] ታሞ እኔ የማላዝንለት ማን ነው? በድሎስ እኔ የማልደነግጥለት ማን ነው?

[30] መመካት የሚገባ ከሆነስ እኔም በመከራዬ እመካለሁ።

[31] ለዘለዓለም ቡሩክ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ሐሰት እንደማልናገር ያውቃል።

[32] በደማስቆ ከተማ ከንጉሥ አርስጣስዮስ በታች የሆነ የአሕዛብ አለቃ ሊይዘኝ ወድዶ የደማስቆን ከተማ ያስጠብቅ ነበር።

[33] በቅርጫትም አድርገው በመስኮቱ በኩል በአጥሩ ላይ አወረዱኝ፤ ከእጁም አመለጥሁ።

ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2 — Chapters