[1] ወንድሞቻችን አሁን ደግሞ ራሳችንን እያመሰገን ልንነግራችሁ እንጀምራለንን? ወይስ እንደ ሌሎች ስለ እኛ ወደ እናንተ ደብዳቤ እንዲጽፉላችሁ፥ ወይስ እናንተ ትጽፉልን ዘንድ የምንሻው አለን?
[2] የእኛስ መጽሐፋችን እናንተ ናችሁ፤ በልባችን ውስጥም ተጽፋችኋል፤ ትታወቃላችሁም፤ ሰውም ሁሉ ያነብባችኋል።
[3] እናንተ ራሳችሁም በእኛ የተላከች የክርስቶስ መልእክት እንደ ሆናችሁ ያውቃሉ፤ ይህቺውም የተጻፈች በሕያው እግዚአብሔር መንፈስ ነው እንጂ በቀለም አይደለም፤ በሥጋ ልብ ሠሌዳነት ነው እንጂ በድንጋይ ሠሌዳም አይደለም።
[4] ነገር ግን በክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ዘንድ እንዲህ ያለ እምነት አለን።
[5] ኀይላችን ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ ከእኛ ከራሳችን እንደ ሆነ አድርገን ምንም ልናስብ አይገባንም።
[6] በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ሕግ አገልጋዮች አደረገን፤ ፊደል ይገድላል፥ መንፈስ ግን ሕያው ያደርጋል። ስለ መልእክታት መበላለጥ
[7] ስለዚያ ስለ አለፈው የፊቱ ብርሃን የእስራኤል ልጆች የሙሴን ፊት መመልከት እስኪሳናቸው ድረስ በዚያች በድንጋይ ላይ በፊደል ለተቀረጸች ለሞት መልእክት ክብር ከተደረገላት፥
[8] ለመንፈስ ቅዱስ መልእክትማ ምንኛ እጅግ ክብር ሊደረግ ይገባ ይሆን?
[9] ኵuነኔን ለምታመጣ መልእክት ብዙ ክብር ከተደረገላት የጽድቅ መልእክትማ ምን ያህል ትከብርና ትመሰገን ይሆን?
[10] በዚህ ፍጹም ክብር ባነጻጸሯት ጊዜ የከበረችው እንዳልከበረች ትሆናለችና።
[11] ያ የሚያልፈው ክብር ካገኘ፥ ያ ጸንቶ የሚኖረውማ እንዴት እጅግ ክብር ያገኝ ይሆን?
[12] እንግዲህ ይህን ያህል ተስፋ ካለን በግልጥ ፊት ለፊት ልንቀርብ እንችላለን።
[13] የዚያን ይሻር የነበረውን መጨረሻ፥ የእስራኤል ልጆች እንዳያዩት ፊቱን ይሸፍን እንደ ነበረው እንደ ሙሴ አይደለም።
[14] ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ ልባቸው ተሸፍኖአል፤ ያም መጋረጃ ብሉይ ኪዳን በተነበበት ዘመን ሁሉ ጸንቶ ኖሮአል፤ ክርስቶስ እስኪያሳልፈው ድረስ አልተገለጠምና።
[15] እስከ ዛሬም የሙሴን ሕግ ሲያነብቡ ያ መጋረጃ ልባቸውን ይሸፍናቸዋል።
[16] ወደ እግዚአብሔር በተመለሱ ጊዜ ግን ያ መጋረጃ ከእነርሱ ይርቃል።
[17] እግዚአብሔር መንፈስ ነውና፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ባለበትም በዚያ ነፃነት አለ።
[18] እኛስ ሁላችን ፊታችንን ገልጠን በመስተዋት እንደሚያይ የእግዚአብሔርን ክብር እናያለን፤ ከእግዚአብሔር መንፈስ እንደ ተሰጠን መጠን የእርሱን አርአያ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንገባለን።