Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:17

[1] በምድር ያለው ማደሪያ ቤታችን ቢፈርስም፥ በሰማይ በእግዚአብሔር ዘንድ የሰው እጅ ያልሠራው ዘለዓለማዊ ቤት እንዳለን እናውቃለን።

[2] ስለ እርሱ የምንደክምለትን በሰማይ ያለውን ቤታችንን እንለብስ ዘንድ እርሱን ተስፋ እናደርጋለን።

[3] ከለበስነውም በኋላ ዕራቐታችንን የምንገኝ አይደለንም።

[4] በዚህ ቤት ውስጥ ሳለንም ከከባድነቱ የተነሣ እጅግ እናዝናለን፤ ነገር ግን ሟች በሕይወት ይዋጥ ዘንድ ሌላ ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ አንወድም።

[5] ለዚህም ያዘጋጀን እግዚአብሔር ነው፤ እርሱም የመንፈስ ቅዱስን ፈለማ ሰጠን።

[6] እንግዲህ ሁልጊዜ እመኑ፥ ጨክኑም፤ በዚህ ሥጋ ሳላችሁም እናንተ እንግዶች እንደ ሆናችሁ ታውቃላችሁ፤ ከሥጋችሁም ተለይታችሁ ወደ ጌታችን ትሄዳላችሁ።

[7] በእምነት እንኖራለን፤ በማየትም አይደለም።

[8] ታምነናል፤ ይልቁንም ከሥጋችን ተለይተን ወደ ጌታችን እንሄዳለንና ደስ ይለናል።

[9] አሁንም ብንኖርም፥ ብንሞትም እርሱን ደስ ለማሰኘት እንጥራለን።

[10] መልካም ቢሆን፥ ክፉም ቢሆን በሥጋችን እንደ ሠራነው ዋጋችንን እንቀበል ዘንድ፥ ሁላችን በክርስቶስ የፍርድ ዙፋን ፊት እንቆማለንና።

[11] እግዚአብሔርን መፍራት ዐውቀን ሰዎችን እናሳምናለን፤ ለእግዚአብሔር ግን እኛ የተገለጥን ነን፤ እንዲሁም በልቡናችሁ የተገለጥን እንደ ሆን እንታመናለን።

[12] በዚህ ደግሞ በእናንተ ዘንድ ራሳችንን የምናመሰግን አይደለም፤ ነገር ግን እኛ እንደምንመካባችሁ፥ እናንተም በእኛ እንድትመኩ፥ ከልብ ሳይሆን ለሰው ይምሰል በሚመኩ ሰዎች ዘንድ መልስ እንዲሆናችሁ ምክንያትን እንሰጣችኋለን።

[13] እኛ ሰነፎች ብንሆንም፥ ስንፍናችን ለእግዚአብሔር ነው፤ ዐዋቂዎች ብንሆንም ዐዋቂነታችን ለእናንተ ነው።

[14] የክርስቶስ ፍቅር በዚህ አሳብ እንድንጸና ያስገድደናል፤ ሁሉ ፈጽመው ስለ ሞቱ አንዱ ስለ ሁሉ ቤዛ ሆኖ ሞቶአልና።

[15] በሕይወት የሚኖሩትም ስለ እነርሱ ቤዛ ሆኖ ለሞተውና ለተነሣውም እንጂ ወደፊት ለራሳቸው የሚኖሩ እንዳይሆኑ እርሱ ስለ ሁሉ ቤዛ ሆኖ ሞተ።

[16] ስለዚህ ከአሁን ጀምሮ በሥጋ የምናውቀው የለም፤ ክርስቶስንም በሥጋ ብናውቀው አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ የምናውቀው አይደለም።

[17] አሁንም በክርስቶስ የሆነው ሁሉ አዲስ ፍጥረት ነው፤ የቀደመውም አለፈ፤ እነሆ ሁሉም አዲስ ሆነ።

[18] ነገር ግን ሁሉ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ከአስታረቀን፥ የማስታረቅ መልእክትንም ከሰጠን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።

[19] ኀጢአታቸውን ይቅር ብሎ በደላቸውንም ሳያስብ እግዚአብሔር በክርስቶስ ዓለሙን ከራሱ ጋር አስታርቆአልና፤ የዕርቅ ቃሉንም በእኛ ላይ አደረገ፤ የይቅርታውንም መልእክት ሰጠን።

[20] እኛስ በክርስቶስ አምሳል እንለምናለን፤ እግዚአብሔርም በእኛ መጽናናትን ይሰጣችኋል፤ ከእግዚአብሔርም ጋር ትታረቁ ዘንድ በክርስቶስ እንለምናችኋለን።

[21] ኀጢአት የሌለበት እርሱ እኛን ለእግዚአብሔር ያጸድቀን ዘንድ ስለ እኛ ራሱን እንደ ኃጥእ አድርጓልና።

ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2 — Chapters