Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 4:01

[1] በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነ ጳውሎስና ከወንድማችን ጢሞቴዎስ በቆሮንቶስ ሀገር ላለችው የእግዚአሔር ቤተ ክርስቲያንና በአካይያ ሀገር ላሉ ቅዱሳን ሁሉ፥

[2] ከአባታችን ከእግዚአብሔርና ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምና ጸጋ ለእናንተ ይሁን።

[3] የምሕረት አባት፥ የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይመስገን።

[4] እግዚአብሔር በአጽናናን በዚያ መጽናናት በመከራ ያሉትን ሁሉ ማጽናናት እንችል ዘንድ ከመከራችን ሁሉ ያጽናናን እርሱ ይመስገን።

[5] የክርስቶስ መከራ በእኛ ላይ እንደ በዛ መጠን እንዲሁ መጽናናታችንም በክርስቶስ ይበዛልና።

[6] መከራ ብንቀበልም እናንተ እንድትድኑና እንድትጽናኑ ነው፤ ብንጽናናም እኛ የተቀበልነውን ያን መከራ በመታገሥ ስለሚደረግ መጽናናታችሁ ነው።

[7] ስለ እናንተ ያለን ተስፋም የጸና ነው፤ መከራችንን እንደ ተካፈላችሁ መጠን፥ እንዲሁ በመጽናናታችንም እንደምትተባበሩ እናውቃለን።

[8] ወንድሞቻችን ሆይ፥ በእስያ መከራ እንደ ተቀበልን ልታውቁ እወዳለሁ፤ ለሕይወታችን ተስፋ እስክንቈርጥ ድረስ ከዐቅማችን በላይ እጅግ መከራ ጸንቶብን ነበርና።

[9] ሙታንን በሚያስነሣቸው በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን በውስጣችን ለመሞት ቈርጠን ነበር።

[10] እርሱም እንዲህ ካለ ሞት አዳነን፤ ያድነንማል፤ አሁንም እንደሚያድነን እርሱን እንታመናለን።

[11] በብዙዎች ጸሎት ጸጋን እናገኝ ዘንድ፥ ብዙዎችም በእኛ ፋንታ ያመሰግኑ ዘንድ እናንተ በጸሎታችሁ ርዱን።

[12] በእግዚአብሔር ቸርነትና ይቅርታ መመኪያችንና የነፃነታችን ምስክር ይህቺ ናትና፥ በሥጋዊ ጥበብ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ጸጋ በዚህ ዓለም፥ ይልቁንም በእናንተ ዘንድ ተመላለስን።

[13] የምታነቡትንና የምታውቁትን ነው እንጂ፥ ሌላ የምንጽፍላችሁ የለምና፥ ይህንም እስከ ፍጻሜ እንደምታስተውሉት ተስፋ አደርጋለሁ።

[14] እኛ መመኪያችሁ እንደሆን፥ እንዲሁ እናንተም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን መመኪያችን እንድትሆኑ በከፊል እንዳወቃችሁ ተስፋ እናደርጋለን።

[15] በዚህም ታምኜ ጸጋን በዕጥፍ እንድታገኙ በመጀመሪያ ወደ እናንተ እመጣ ዘንድ መከርሁ።

[16] በእናንተም በኩል ወደ መቄዶንያ እንዳልፍ፥ ዳግመኛም ከመቄዶንያ እንድመለስና እናንተም ደግሞ ወደ ይሁዳ ሀገር ትሸኙኝ ዘንድ መከርሁ።

[17] እንግዲህ ይህን የመከርሁ በውኑ የሠራሁት እንደ አላዋቂ ሰው ሆኜ ነውን? ወይስ በእኔ በኩል አዎን አዎን፥ አይደለም አይደለም ማለት እንዲሆን ያን የምመክረው ለሰው ይምሰል ነውን?

[18] እግዚአብሔር የታመነ ነው፤ ለእናንተም የሚነገረው ቃላችን እውነትና ሐሰት አልተቀላቀለበትም።

[19] እኛ ማለት እኔ ጳውሎስ፥ ስልዋኖስና ጢሞቴዎስ የሰበክንላችሁ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነትና ሐሰት አይደለም፤ ነገር ግን ስለ እርሱ ያስተማርነው እውነት ነው።

[20] እግዚአብሔር የሰጠው ተስፋ ሁሉ በክርስቶስ እውነት ሆኖአልና፤ ስለዚህም በእርሱ ለእግዚአብሔር ክብር አሜን እንላለን።

[21] ከእናንተ ጋር በክርስቶስ ስም የሚያጸናንና የቀባን እግዚአብሔር ነው።

[22] ደግሞም ያተመንና የመንፈስ ቅዱስን ፈለማ በልቡናችን የሰጠን እርሱ ነው።

[23] እኔ ለእናንተ በመራራት ወደ ቆሮንቶስ እንዳልመጣሁ፥ ስለ ራሴ እግዚአብሔርን ምስክር አደርገዋለሁ።

[24] ደስ የሚላችሁን እንድታደርጉ እንረዳችኋለን እንጂ እንድታምኑ ግድ የምንላችሁ አይደለም፤ በእምነት ቆማችኋልና።

ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2 — Chapters