Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:03

[1] ወንድሞቻችን ሆይ፥ እኔ ጳውሎስ በእናንተ ዘንድ ፊት ለፊት ሳለሁ ትሑት የሆንሁ፥ ከእናንተ ብርቅ ግን የምደፍራችሁ በክርስቶስ የዋህነትና ቸርነት እማልዳችኋለሁ፥ በፍቅራችሁ እታመናለሁና።

[2] ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ እሠራለሁ፤ በሥጋዊ ሥርዐትም እንደምንኖር አድርገው በሚጠረጥሩን ሰዎች ላይ በድፍረት ለመናገር አስባለሁ፤ እናንተ ግን በዚህ ዓይነት ድፍረት እንድናገር እንዳታደርጉኝ እለምናችኋለሁ።

[3] በሥጋችንስ እንሄዳለን፤ ነገር ግን በእርሱው ሥርዐት የምንሄድና የምንዋጋ አይደለም።

[4] የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ጽኑ ምሽግን በሚያፈርስ በእግዚአብሔር ኀይል ነው እንጂ።

[5] ልብ ሁሉ ይማረክ ዘንድ ኅሊናም ለክርስቶስ ይገዛ ዘንድ በእግዚአብሔር ላይ የሚታበየውንና ከፍ ከፍ የሚለውን እናፈርሳለን።

[6] እናንተ ትእዛዝን በፈጸማችሁ ጊዜ የማይገዛውን ሁሉ እኛ ልንበቀለው ዝግጁዎች ነን።

[7] በፊታችሁ ያለውን ተመልከቱ፤ ማንም በክርስቶስ ያመነ ቢሆን፥ ይህን እንደ ገና በራሱ ይቐጠረው፤ እርሱ የክርስቶስ እንደ ሆነ እኛም እንዲሁ ነንና።

[8] እናንተን ለማነጽ እንጂ፥ እናንተን ለማፍረስ ያይደለ፥ እግዚአብሔር በእናንተ ላይ በሰጠን ሥልጣን እጅግ የተመካሁት መመካት ቢኖር አላፍርም።

[9] ነገር ግን በመልእክቶቼ የማስፈራራችሁ እንዳይመስላችሁ፥ ይህን ትምክሕቴን እተወዋለሁ።

[10] ከሰዎች መካከል “መልእክቶቹ ከባዶችና አስጨናቂዎች ናቸው፤ ሰውነቱ ግን ደካማ ነው፤ ነገሩም ተርታ ነው ” የሚሉ አሉና።

[11] ነገር ግን ይህን ነገር የሚናገር ይህን ይወቅ፤ በሌለንበት ጊዜ በመልእክታችን እንደ ተገለጠው እንደ ቃላችን፥ ባለንበትም ጊዜ በሥራችን እንዲሁ ነን።

[12] እነርሱ ራሳቸውን በአሰቡትና በገመገሙት መጠን ራሳቸውን ከሚያመሰግኑት ሰዎች ጋር ራሳችንን ልንቈጥር፥ ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርም፤ እነርሱ ራሳቸውም የሚናገሩትን ትርጕuሙን አያውቁትም።

[13] እኛስ ወደ እናንተ እስክንደርስ ድረስ እግዚአብሔር በወሰነልን ሕግና ሥርዐት እንጂ፥ ከዐቅማችን አልፈን እጅግ አንመካም።

[14] ወደ እናንተ እንደማንደርስ አድርገን፥ ራሳችንን የምናመሰግን አይደለምና፤ ነገር ግን የክርስቶስን ሕግ በማስተማር ወደ እናንተ ደርሰናል።

[15] እኛስ በማይገባ ሌላ በደከመበት አንመካም፤ ነገር ግን ሃይማኖታችሁ እንድትሰፋ፥ የተሠራችላችሁ ሕግም በእናንተ እንድትጸና ተስፋ እናደርጋለን።

[16] አብዝተንም እናስተምራችኋለን፤ ያንጊዜም መጠናችን ከሥራችን ጋር ከፍ ከፍ ይላል፤ እኛስ ቀና ባልሆነውና በማይገባው አንመካም።

[17] “የሚመካ ግን በእግዚአብሔር ይመካ።”

[18] እግዚአብሔር ያከበረው ብቻ ይከብራል እንጂ ራሱን የሚያከብር የተመረጠ አይደለም።

ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2 — Chapters