[1] ወንድሞቻችን ሆይ፥ እንግዲህ ይህ ተስፋ ያለን ስለሆን ራሳችንን እናንጻ፤ ሥጋችንን አናርክስ፤ ነፍሳችንንም አናሳድፍ፤ እግዚአብሔርንም በመፍራት የምንቀደስበትን እንሥራ።
[2] አሁንም ወንድሞቻችን ሆይ፥ ታገሡን፥ የበደልነው የለም፤ የገፋነውም የለም፤ ያጠፋነውም የለም፤ የቀማነውም የለም።
[3] ይህንም የምለው በእናንተ ለመፍረድ አይደለም፤ ለሞትም፥ ለሕይወትም ቢሆን እናንተ በልባችን እንዳላችሁ ፈጽሜ ተናግሬአለሁና።
[4] በእናንተ ዘንድ እንዲሁ ብዙ መወደድ አለኝ፤ ስለ እናንተም የምመካበት ብዙ ነው፤ መጽናናትንም አገኘሁ፤ ከመከራዬም ሁሉ ይልቅ ደስታዬ በዛልኝ።
[5] ወደ መቄዶንያም በደረስን ጊዜ ለሰውነታችን ጥቂት ስንኳን ዕረፍት አላገኘንም፤ በሁሉም መከራ አጸኑብን እንጂ፤ በውጭም መጋደል ነበር፤ በውስጥም ፍርሀት ነበር።
[6] ነገር ግን ያዘኑትን የሚያጽናና እርሱ እግዚአብሔር በቲቶ መምጣት አጽናናን።
[7] በመምጣቱ ብቻ አይደለም፤ በአጽናናችሁት ማጽናናትም ነው እንጂ፤ ለእኛ እንደምታስቡና እንደምትቀኑ ፍቅራችሁን ነግሮናል፤ ይህንም ሰምቼ ደስታዬ በእናንተ በዛ።
[8] መጀመሪያ በጻፍሁት መልእክት ባሳዝናችሁም እንኳ አያጸጽተኝም፤ ብጸጸትም፥ እነሆ ያች መልእክት ለጥቂት ጊዜ ብቻ እንዳሳዘነቻችሁ አያለሁ።
[9] አሁን ግን እኔ ስለ እርሷ በብዙ ደስ ይለኛል፤ ደስታዬም ስለ አዘናችሁ አይደለም፤ ንስሓ ልትገቡ ስለ አዘናችሁ እንጂ፤ ከእናንተ አንዱ ስንኳ እንዳይጠፋ፥ ስለ እግዚአብሔር ብላችሁ አዝናችኋልና።
[10] ስለ እግዚአብሔር ተብሎ የሚደረግ ኀዘን የዘለዓለም ሕይወትን የሚያሰጥ ንስሓ ነው። ስለ ዓለም የሚደረግ ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል።
[11] እነሆ፥ ያ ስለ እግዚአብሔር ብላችሁ ያደረጋችሁት ኀዘን ምንም የማታውቁ እስከ መሆን ደርሳችሁ፥ ራሳችሁን በበጎ ሥራና በንጽሕና እስክታጸኑ ድረስ፥ ትጋትንና ክርክርን፥ ቐጣንና ፍርሀትን፥ ናፍቆትንና ቅንዐትን፥ በቀልንም አደረገላችሁ፤
[12] ይህን የጻፍሁላችሁ በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ እንደ ተጋችሁ ይታወቅ ዘንድ ነው እንጂ ስለ በደለና ስለ ተበደለ ሰው አይደለም።
[13] ስለዚህም ተጽናንተናል፤ በመጽናናታችንም ስለ ቲቶ ደስታ አብልጦ ደስ አለን፤ በሁላችሁ ዘንድ ሰውነቱን አሳርፋችኋታልና።
[14] ስለ እናንተ ለእርሱ በተመካሁበት ሁሉ አላሳፈራችሁኝምና፤ ነገር ግን ሁሉን ለእናንተ በእውነት እንደ ተናገርን፥ እንደዚሁ ደግሞ በቲቶ ፊት ትምክህታችን እውነት ሆነ።
[15] ስለዚህም እጅግ ያመሰግናችኋል፤ እንደ ታዘዛችሁለት፥ በመፍራትና በመደንገጥም እንደ ተቀበላችሁት ያስባችኋል።
[16] እኔም በሁሉ ነገር እተማመናችኋለሁና ደስ ይለኛል።