[1] ከእርሱም ጋር አብረን እየሠራን፥ የተቀበላችኋትን የእግዚአብሔር ጸጋ ለከንቱ እንዳታደርጓት እንማልዳችኋለን።
[2] እንዲህ ብሎአልና ፥ “በተመረጠችው ቀን ሰማሁህ፤ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ” እነሆ፥ የተመረጠችው ቀን ዛሬ ናት።
[3] አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ፥ በአንዳች ነገር ማሰናከያ እንዳንሰጥ እንጠንቀቅ።
[4] ነገር ግን በሁሉ ራሳችንን አቅንተን፥ የእግዚአብሔር አገልጋዮች እንሁን፤ በብዙ ትዕግሥትና በመከራ፥ በችግርና በጭንቀት ሁሉ፥
[5] በመገረፍና በመታሰር፥ በድካምና በመታወክ፥ በመትጋትና በመጿም፥
[6] በንጽሕናና በዕውቀት፥ በምክርና በመታገሥ፥ በቸርነትና በመንፈስ ቅዱስ፥ አድልዎ በሌለበት ፍቅር፥
[7] በእውነት ቃል፥ በእግዚአብሔር ኀይል ለቀኝና ለግራ በሚሆን የጽድቅ የጦር ዕቃ፥
[8] በክብርና በውርደት፥ በምርቃትና በርግማን፥ እንደ አሳቾች ስንታይ እውነተኟች ነን።
[9] እንደማይታወቁ ስንታይ የታወቅን ነን፤ እንደ ሰነፎች ስንታይም ልባሞች ነን፤ እንደ ሙታን ስንታይ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆንም አንገደልም።
[10] ኀዘንተኟች ስንሆን ዘወትር ደስተኟች ነን፤ እንደ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን እናበለጽጋለን፤ ምንም የሌለን ስንሆን ሁሉ በእጃችን ነው።
[11] የቆሮንቶስ ሰዎች ሆይ፥ ለእናንተ አፋችን የተከፈተ ነው፤ ልባችንም የሰፋ ነው።
[12] ከእናንተ የደረሰ ኀዘን በእኛ የለም፤ ከእኛም በእናንተ ላይ የደረሰ ኀዘን የለም፤ ነገር ግን በልባችሁ አዝናችኋል።
[13] ልጆቼ እንደ መሆናችሁ፥ ይህን እላችኋለሁ፤ ከእናንተ ላይ ስለሚገባኝ ብድራቴ እናንተ ፍቅራችሁን አስፉልኝ።
[14] ተጠራጣሪዎች አትሁኑ፤ ወደማያምኑ ሰዎች አንድነትም አትሂዱ፤ ጽድቅን ከኀጢአት ጋር አንድ የሚያደርጋት ማን ነው? ብርሃንንስ ከጨለማ ጋር የሚቀላቅል ማን ነው?
[15] ክርስቶስን ከቤልሆር ጋር አንድ የሚያደርገው ማን ነው? ወይስ ምእመናንን ከመናፍቃን ጋር አንድ ወገን የሚያደርጋቸው ማን ነው?
[16] የእግዚአብሔርን ታቦትስ በጣዖት ቤት ውስጥ የሚያኖር ማን ነው? የሕያው እግዚአብሔር ማደሪያዎች እኛ አይደለንምን? እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረ ፥ “እኔ በእነርሱ አድራለሁ፤ በመካከላቸውም እኖራለሁ፤ አምላካቸውም እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆኑኛል።”
[17] ስለዚህም “ከመካከላቸው ተለይታችሁ ውጡ፤ ከእነርሱም ተለዩ፤ ወደ ርኩሳንም አትቅረቡ፥ እኔም እቀበላችኋለሁ።
[18] አባት እሆናችኋለሁ፤ እናንተም ወንዶችና ሴቶች ልጆች ትሆኑኛላችሁ አለ ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር።”