[1] ወንድሞቻችን ሆይ፥ ከእናንተ ወገን የተሳሳተ ሰው ቢኖር በመንፈስ ቅዱስ የጸናችሁ እናንት እንዳትሳሳቱ ለራሳችሁ እየተጠበቃችሁ፥ እንደዚህ ያለውን ሰው ቅንነት ባለው ልቡና አጽኑት።
[2] ከእናንተ እያንዳንዱ የባልንጀራውን ሸክም ይሸከም፤ በዚህም የክርስቶስን ሕግ ትፈጽማላችሁ።
[3] አንዱም ምንም ሳይሆን ምንም የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና።
[4] ለሌላ ያይደለ ለራሱ መመኪያ እንዲሆነው ሁሉም ሥራዉን ይመርምር።
[5] ሁሉም ሸክሙን ይሸከማልና።
[6] ይህንም ነገር ንኡሰ ክርስቲያን ይስማው፤ መልካሙንም ነገር ሁሉ ከሚያስተምረው ይማር።
[7] አያስቱአችሁ፤ በእግዚአብሔርም የሚዘብት አይኑር፤ ሰውም የሚዘራውን ያጭዳል።
[8] በሥጋው የሚዘራ ሞትን ያጭዳል፤ በመንፈሱም የሚዘራ የዘለዓለም ሕይወትን ያጭዳል።
[9] በጎ ሥራ መሥራትን ቸል አንበል፥ በጊዜው እናገኘዋለንና።
[10] እንግዲህ ጊዜ ሳለን ለሁሉ መልካም ሥራ እናድርግ፤ ይልቁንም ለሃይማኖት ሰዎች።
[11] በእጄ እንደ ጻፍሁላችሁ እዩ።
[12] ለሰው ፊት ሊያደሉ የሚወዱ እነዚያ እንድትገዘሩ ያስገድዱአችኋል፤ ነገር ግን የክርስቶስን መስቀል እንዳትከተሉ ነው።
[13] የተገዘሩትም ቢሆኑ በሰውነታችሁ እንደምትመኩ ልትገዘሩ ይወዳሉ እንጂ ኦሪትን አልጠበቁም።
[14] እኔ ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እንጂ በሌላ አልመካም፤ በእኔ ዘንድ ዓለሙ የሞተ ነው፥ እኔም በዓለሙ ዘንድ የሞትሁ ነኝ።
[15] በኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ አዲስ ፍጥረት መሆን ነው እንጂ መገዘር አይጠቅምም፤ አለመገዘርም ግዳጅ አይፈጽምም።
[16] ይህን ሕግ ለሚፈጽሙ ሰዎች ሰላምና ይቅርታ ይሁን፤ የእግዚአብሔር ወገኖች በሆኑ በእስራኤል ላይም ይሁን።
[17] እንግዲህ ወዲህስ የሚያደክመኝ አይኑር፤ እኔ የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ በሥጋዬ እሸከማለሁ።
[18] ወንድሞቼ ሆይ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን። በሮሜ ተጽፋ በቲቶ እጅ ወደ ገላትያ ሰዎች የተላከች መልእክት ተፈጸመች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ አሜን።