[1] ነገር ግን እላለሁ፤ ወራሹ ሕፃን ሳለ ለሁሉ ጌታ ሲሆን ከአገልጋይ የሚለይ አይደለም።
[2] ነገር ግን አባቱ እስከ ቀጠረለት ዕድሜ ድረስ በአያት ወይም በሞግዚት እጅ ይጠበቃል።
[3] እንዲሁ እኛም ሕፃናት በነበርን ጊዜ፥ ለዚህ ዓለም ስሕተት ተገዝተን ነበር።
[4] ነገር ግን ቀጠሮው በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ፤ ከሴትም ተወለደ፤ የኦሪትንም ሕግ ፈጸመ።
[5] እኛ የልጅነትን ክብር እንድናገኝ በኦሪት የነበሩትን ይዋጅ ዘንድ።
[6] ልጆች እንደ መሆናችሁ መጠን እግዚአብሔር አባ አባቴ ብላችሁ የምትጠሩትን የልጁን መንፈስ በልባችሁ አሳደረ።
[7] እንኪያስ እናንተ ልጆች ናችሁ እንጂ ባሮች አይደላችሁም፤ ልጆች ከሆናችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሾች ናችሁ።
[8] ነገር ግን ቀድሞ እግዚአብሔርን ባለማወቃችሁ፥ በባሕርያቸው አማልክት ላልሆኑ ተገዝታችሁ ነበር።
[9] ዛሬ ግን እግዚአብሔርን ዐወቃችሁት፤ ይልቁንም እርሱ ዐወቃችሁ፤ እንደ ገና ደግሞ ወደዚያ ወደ ደካማው፥ ወደ ድሀው ወደዚህ ዓለም ጣዖት ተመልሳችሁ፥ ትገዙላቸው ዘንድ እንዴት ፈጠራን ትሻላችሁ?
[10] ዕለትንና ወርን፥ ጊዜንና ዓመታትን ትጠብቃላችሁ።
[11] ስለ እናንተ በከንቱ ደክሜ እንደ ሆነ ብዬ እፈራችኋለሁ።
[12] ወንድሞቻችን ሆይ፥ እኔ ደግሞ እንደ እናንተ ሁኛለሁ፤ እንደ እኔ ሁኑ ብዬ እማልዳችኋለሁ፤ አንዳች አልበደላችሁኝምና።
[13] መጀመሪያ ወንጌልን በሰበክሁላችሁ ጊዜ፥ ከሥጋ ድካም የተነሣ እንደ ነበር ታውቃላችሁ።
[14] መከራ እቀበል በነበረበት ጊዜ አልሰለቻችሁኝም፤ እንደ እግዚአብሔር መልአክ፥ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስም ተቀበላችሁኝ እንጂ በሰውነቴ አልናቃችሁኝም።
[15] አሁንስ ደስ ማሰኘታችሁ ወዴት አለ? ቢቻላችሁስ ዐይናችሁንም እንኳ ቢሆን አውጥታችሁ ትሰጡኝ እንደ ነበረ፥ እኔ ምስክራችሁ ነኝ።
[16] እውነቱን ስለ ነገርኋችሁ ባላጋራ ሆንኋችሁን?
[17] እነዚያማ ይቀኑባችኋል፤ ነገር ግን በእነርሱ ላይ እንድትቀኑ ሊዘጉአችሁ ይወዳሉ እንጂ ለመልካም አይደለም።
[18] መቅናትስ ዘወትር ለመልካም ሥራ ልትቀኑ ይገባል፤ ነገር ግን እኔ ከእናንተ ዘንድ ባለሁበት ጊዜ ብቻ አይደለም።
[19] ልጆቼ፥ እንደ ገና የምጨነቅላችሁ ክርስቶስ በልባችሁ እስኪሣልባችሁ ድረስ ነው።
[20] ቃሌን ለውጬ አሁን በእናንተ ዘንድ ልገኝ እሻለሁ፤ ስለ እናንተ የምናገረውን አጣለሁና።
[21] በኦሪት ሕግ እንኑር ትላላችሁን? ኦሪትን አትሰሙአትምን?
[22] አብርሃም ሁለት ልጆችን አንዱን ከባሪያዪቱ፥ አንዱንም ከእመቤቲቱ እንደ ወለደ ተጽፎአልና።
[23] ነገር ግን ከባሪያዪቱ የተወለደው ልደቱ ልዩ ነው፤ በሰው ልማድ ተወለደ፤ ከእመቤቲቱ የተወለደው ግን እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ ተወለደ።
[24] ይህም የሁለቱ ሥርዐት ምሳሌ ነው፤ አንዲቱ ከደብረ ሲና ለባርነት ትወልዳለች፤ እርስዋም አጋር ናት።
[25] አጋርም በዐረብ ሀገር ያለች ደብረ ሲና ናት፤ ከዛሬዪቱ ኢየሩሳሌም ጋር ትነጻጸራለች፤ ከልጆችዋ ጋርም ትገዛለች።
[26] የላይኛዪቱ ኢየሩሳሌም ግን በነፃነት የምትኖር ናት፤ እርስዋም እናታችን ናት።
[27] “የማትወልድ መካን ደስ ይላታል፤ ምጥ የማታውቀውም ደስ ብሎአት እልል ትላለች፤ ባል ካላት ይልቅ የፈቲቱ ልጆች ብዙዎች ናቸውና” ተብሎ ተጽፎአል።
[28] ወንድሞቻችን ሆይ፥ እኛስ እንደ ይስሐቅ የተስፋ ልጆች ነን።
[29] ነገር ግን በሥጋ ልማድ የተወለደው በመንፈሳዊ ግብር የተወለደውን በዚያ ጊዜ እንዳሳደደው ዛሬም እንዲሁ ነው።
[30] ነገር ግን መጽሐፍ ምን ይላል? “የባሪያዪቱ ልጅ ከእመቤቲቱ ልጅ ጋር አይወርስምና ባሪያዪቱን ከልጅዋ ጋር አስወጥተህ ስደዳት ”
[31] ወንድሞቻችን ሆይ፥ አሁንም እኛ የእመቤቲቱ ነን እንጂ የባሪያዪቱ ልጆች አይደለንም፤ ክርስቶስ ነጻ አውጥቶናልና።