Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:38

[1] ከዐሥራ አራት ዓመትም በኋላ ከበርናባስ ጋር እንደ ገና ወደ ኢየሩሳሌም ወጣሁ፤ ቲቶንም ይዠው ሄድሁ።

[2] እንደ ተገለጠልኝም ወጣሁ፤ በከንቱ እንዳልሮጥ፥ ወይም በከንቱ ሮጬ እንዳልሆነ፥ በአሕዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል አለቆች መስለው ለሚታዩት አስታወቅኋቸው።

[3] አብሮኝ የነበረው ቲቶም አረማዊ ሲሆን እንዲገዘር ግድ አላልሁትም።

[4] ይኸውም ባሪያዎች ያደርጉን ዘንድ በኢየሱስ ክርስቶስ ያገኘናትን ነጻነት ሊሰልሉ በስውር ወደ እኛ የገቡ ሐሰተኟች መምህራንን ደስ አይበላቸው ብዬ ነው።

[5] ለምንም ይሆናሉ ብለን የማናስባቸው ናቸው፤ እውነተኛው ትምህርት በእናንተ ይጸና ዘንድ አንዲት ሰዓትም እንኳ አልተገዛንላቸውም።

[6] አለቆች የመሰሉት ግን ቀድሞ እነርሱ እንዴት እንደ ነበሩ ልናገር አያገደኝም፤ እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያዳላምና፤ አለቆች የመሰሉትም ከራሳቸው ምንም ነገር የጨመሩልኝ የለምና።

[7] የጴጥሮስ ትምህርት በተገዘሩ በአይሁድ ዘንድ እንደ ታመነለት፥ የእኔም ትምህርት ባልተገዘሩ በአሕዛብ ዘንድ እንደ ታመነ ዐውቀዋል እንጂ።

[8] ወደ ተገዘሩ አይሁድ በተላከ ጊዜ ጴጥሮስን የረዳው እርሱ እኔንም ባልተገዘሩ አሕዛብ ዘንድ ረዳኝ።

[9] የሰጠኝንም ጸጋ ዐውቀው አዕማድ የሚሏቸው ያዕቆብና ኬፋ፥ ዮሐንስም እኛ ወደ አሕዛብ፥ እነርሱም ወደ አይሁድ እንድንሄድ ለእኔና ለበርናባስ ቀኝ እጃቸውን ሰጡን።

[10] ይልቁንም ነዳያንን እንድናስባቸው ነው፤ ስለዚህም ይህን ነገር ልፈጽመው ተጋሁ።

[11] ነገር ግን ኬፋ ወደ አንጿኪያ በመጣ ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወምሁት፤ ነቅፈውት ነበርና።

[12] ሰዎች ከያዕቆብ ዘንድ ከመምጣታቸው በፊት፥ ከአረማውያን ጋር ይበላ ነበርና፥ በመጡ ጊዜ ግን ተለያቸው፤ ከአይሁድ ወገን የሆኑትን ፈርቶአልና።

[13] ከአይሁድ ወገንም ወደዚህ ግብር የተመለሱ ብዙዎች ነበሩ፤ በርናባስም እንኳ በግብዝነታቸው ተባበረ።

[14] ነገር ግን ወደ እውነተኛው ወንጌል እግራቸውን እንዳላቀኑ ባየሁ ጊዜ፥ በሰው ሁሉ ፊት ኬፋን እንዲህ አልሁት ፥ “አንተ አይሁዳዊ ስትሆን በአይሁድ ሥርዐት ያይደለ፥ በአረማውያን ሥርዐት የምትኖር ከሆነ እንግዲህ አይሁድ እንዲሆኑ አረማውያንን ለምን ታስገድዳቸዋለህ?”

[15] እኛ በትውልዳችን አይሁድ ነን፤ ኀጢአተኟች የሆኑ አሕዛብም አይደለንም።

[16] ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንጂ የኦሪትን ሥራ በመሥራት እንደማይጸድቅ እናውቃለንና፤ እኛም የኦሪትን ሥራ በመሥራት ሳይሆን በእርሱ በማመናችን እንጸድቅ ዘንድ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነናል፤ ሰው ሁሉ በኦሪት ሥራ አይጸድቅምና።

[17] በክርስቶስ ልንጸድቅ የምንሻ እኛ እንደ ኀጢአተኟች ከሆን እንግዲህ ክርስቶስ የኀጢአት አገልጋይ መሆኑ ነውን? አይደለም።

[18] ያን ያፈረስሁትን መልሼ የማንጽ ከሆነ ራሴን ሕግ አፍራሽ አደረግሁ።

[19] እኔስ ለእግዚአብሔር ሕያው ሆኜ በሁለተኛው ሕግ እኖር ዘንድ ከቀደመው ሕግ ተለየሁ።

[20] ከክርስቶስ ጋርም ተሰቀልሁ፤ ሕይወቴም አለቀች፤ ነገር ግን በክርስቶስ ሕይወት አለሁ፤ ዛሬም በሥጋዬ የምኖረውን ኑሮ የወደደኝን ስለ እኔም ራሱን አሳልፎ የሰጠውን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመን እኖራለሁ።

[21] የእግዚአብሔርንም ጸጋ አልክድም፤ የኦሪትን ሥራ በመሥራት የሚጸድቁ ከሆነ እንኪያስ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ።

ወደ ገላትያ ሰዎች። — Chapters