Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 4:24

[1] እናንተ ሰነፎች የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ ለዐይን በሚታየው እውነት እንዳታምኑ ማን አታለላችሁ? እርሱም እንዲሰቀል አስቀድሞ የተጻፈለት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

[2] በእናንተ ዘንድ ይህን ብቻ ላውቅ እወድዳለሁ፤ መንፈስ ቅዱስን የተቀበላችሁ የኦሪትን ሥራ በመሥራት ነውን? ወይስ ሃይማኖትን በመስማት?

[3] እንዲህን ሰነፎች ናችሁን? የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ከጀመራችሁ በኋላ የሥጋን ሕግ ልትሠሩ ትመለሳላችሁን?

[4] ይህን ያህል መከራ ተቀብላችሁ፥ ለከንቱ አደረጋችሁት።

[5] እርሱ መንፈስ ቅዱስን የሚሰጣችሁ፥ ኀይልንም የሚያደርግላችሁ የኦሪትን ሥራ በመሥራት ነውን? ወይስ ሃይማኖትን በመስማት ነው?

[6] አብርሃም በእግዚአብሔር እንደ አመነ፥ ጽድቅም ሆኖ እንደ ተቈጠረለት፥

[7] እንግዲህ ያመኑት የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ ታውቃላችሁ።

[8] እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንደሚያጸድቃቸው መጽሐፍ አስቀድሞ ገልጦአልና፤ አሕዛብም ሁሉ በእርሱ እንዲባረኩ እግዚአብሔር አስቀድሞ ለአብርሃም ተስፋ ሰጠው።

[9] አሁንም የሚያምኑ ከአመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ።

[10] በኦሪት ሕግ ያሉ ሁሉ በእርግማን ውስጥ ይኖራሉ፤ መጽሐፍ እንዲህ ብሎአልና ፥ “በዚህ በኦሪት መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈውን ሁሉ የማይፈጽምና የማይጠብቅ ርጉም ይሁን።”

[11] የኦሪትን ሥራ በመሥራትስ በእግዚአብሔር ዘንድ እንደማይጸድቁ ይታወቃል፤ “ጻድቅ ግን በእምነት ይድናል ” ተብሎ ተጽፎአል።

[12] ኦሪትስ ሠርቶ የፈጸመ ይኖርበታል እንጂ በእምነት የሚያጸድቅ አይደለም።

[13] እኛንስ ክርስቶስ ስለ እኛ የኦሪትን መርገም በመሸከሙ ከኦሪት መርገም ዋጅቶናል፤ መጽሐፍ እንዲህ ብሎአልና ፥ “በእንጨት ላይ የተሰቀለ ሁሉ ርጉም ነው።”

[14] እኛ በክርስቶስ አምነን የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ እንድናገኝ የአብርሃም በረከት በኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አሕዛብ ይመለስ ዘንድ።

[15] ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ሰው ልማድ እንናገራለን፤ ሰውም እንኳን የጸናውን ኪዳን አይንቅም አይጨምርበትምም።

[16] እግዚአብሔርም ለአብርሃም ፥ “ለአንተና ለዘርህ ” ብሎ ተስፋ ሰጠው፤ ለብዙዎች እንደሚናገር አድርጎ ለአንተና ለዘሮችህ አላለውም፤ ለአንድ እንደሚናገር አድርጎ ፥ “ለዘርህ ” አለው እንጂ ይኸውም ክርስቶስ ነው።

[17] እንግዲህ እንዲህ እላለሁ ፥ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ይህ ኪዳን ጽኑዕ ነው፤ ከዚህም በኋላ በአራት መቶ ሠላሳ ዓመት ኦሪት መጣች፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ ልትከለክል አይደለም።

[18] መውረስ የኦሪትን ሕግ በመሥራት ከሆነ እንግዲህ በሰጠው ተስፋ አይደለማ፤ እነሆ እግዚአብሔር አስቀድሞ ለአብርሃም ተስፋውን ሰጠው።

[19] ታዲያ ኦሪት ለምን ተሠራች? ኦሪትስ ኀጢአትን ታበዛት ዘንድ፥ ተስፋ ያደረገለት ያ ዘር እስኪመጣ ድረስ፥ በመላእክት በኩል በመካከለኛው እጅ ወረደች።

[20] መካከለኛው ግን ማንም አይደለም፤ አንድ እግዚአብሔር ነው እንጂ።

[21] እንግዲህ ኦሪት እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ ልትከለክል መጣችን? አይደለም፤ ማዳን የሚቻለው ሕግ ተሠርቶ ቢሆንማ፥ በእውነት በዚያ ሕግ ጽድቅ በተገኘ ነበር።

[22] ነገር ግን ተስፋ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ይሆን ዘንድ፥ ያመኑትም ያገኙት ዘንድ፥ መጽሐፍ ሁሉን በኀጢአት ዘግቶታል።

[23] እምነት ሳይመጣ ኦሪት ጠበቀችን፤ ወደሚመጣውም እምነት መራችን።

[24] እንግዲህ ኦሪት በእርሱ በማመን እንጸድቅ ዘንድ ወደ ክርስቶስ መሪ ሆነችን።

[25] እንግዲህ እምነት ከመጣች መሪ አንሻም።

[26] በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ሁላችን የእግዚአብሔር ልጆች ሆነናልና።

[27] በክርስቶስ የተጠመቃችሁ እናንተማ ክርስቶስን ለብሳችኋል።

[28] በዚህም አይሁዳዊ፥ ወይም አረማዊ የለም፤ ገዢ፥ ወይም ተገዢ የለም፤ ወንድ፥ ወይም ሴት የለም፤ ሁላችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ናችሁና።

[29] ለኢየሱስ ክርስቶስ ከሆናችሁም እንግዲህ ተስፋውን የምትወርሱ የአብርሃም ዘር እናንተ ናችሁ።

ወደ ገላትያ ሰዎች። — Chapters