[1] በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና ከሙታን ለይቶ በአስነሣው በእግዚአብሔር አብ ነው እንጂ ከሰዎች ወይም በሰው ሐዋርያ ካልሆነ ከጳውሎስ፥
[2] አብረውኝ ካሉ ከወንድሞቻችንም፥ በገላትያ ላሉ አብያተ ክርስቲያን፤
[3] ከአባታችን ከእግዚአብሔር፥ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስም ሰላምና ጸጋ ለእናንተ ይሁን።
[4] በክፉ ከሚቃወም ከዚህ ዓለም ያድነን ዘንድ በአባታችን በእግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ኀጢአታችን ራሱን አሳልፎ ሰጠ።
[5] ለእርሱ ክብር ይሁን፤ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም አሜን።
[6] በጸጋዉ የጠራችሁን ክርስቶስን ከማመን ወደ ልዩ ወንጌል እንዴት ፈጥነው እንዳስወጧችሁ አደንቃለሁ።
[7] እርሱ ግን ሌላ አይደለም፤ የሚያውኳችሁ ከክርስቶስም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አሉ እንጂ።
[8] እናንተ ግን የእኛን ፍለጋ ተከተሉ፤ እናንተስ እኛም ብንሆን ወይም መልአክ ከሰማይ ወርዶ እኛ ካስተማርናችሁ ወንጌል ሌላ ቢሰብክላችሁ ውጉዝ ይሁን።
[9] አስቀድሜ እንደ አልሁ አሁንም ደግሞ እላለሁ ፥ ካስተማርናችሁ ሌላ ትምህርት ያስተማራችሁ ቢኖር ውጉዝ ይሁን።
[10] አሁንስ ለእግዚአብሔር ያይደለ ለሰው ብዬ አስተምራለሁን? ወይስ ሰውን ደስ አሰኛለሁን? ሰውን ደስ ላሰኝ ብወድስ የክርስቶስ ባሪያ አይደለሁም።
[11] ወንድሞቻችን ሆይ፥ ያስተማርኋችሁ ወንጌል ስለ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ።
[12] ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ገለጠልኝ እንጂ፥ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም፤ አልተማርሁትምም።
[13] በአይሁድ ሥርዐት ውስጥ በነበርሁ ጊዜ፥ የነበረውን የቀድሞ ሥራዬን ሰምታችኋል፤ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እጅግ አሳድድና መከራ አጸናባቸው ነበር።
[14] ለአባቶቼ ሥርዐት እጅግ ቀናተኛ ነበርሁና በወገኖቼ ዘንድ ከጓደኟቼ ሁሉ በአይሁድ ዘንድ እጅግ ከበርሁ።
[15] ከእናቴ ማኅፀን ለይቶ ያወጣኝ እግዚአብሔር በወደደ ጊዜ በጸጋው ጠራኝ።
[16] በስሙም ለአሕዛብ ወንጌልን አስተምር ዘንድ፥ በእጄም የልጁ ክብር ይታወቅ ዘንድ ልጁን ገለጠልኝ፤ ያንጊዜም ከሥጋዊና ከደማዊ ሰው ጋር አልተማከርሁም።
[17] ከእኔ በፊት ወደ ነበሩት ወደ ሐዋርያትም ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፤ ነገር ግን ወደ ዐረብ ሀገር ሄድሁ፤ ዳግመኛም ወደ ደማስቆ ተመለስሁ።
[18] ከሦስት ዓመት በኋላ ግን ኬፋን ላየው ወደ ኢየሩሳሌም ወጣሁ፤ በእርሱ ዘንድም ዐሥራ አምስት ቀን ሰነበትሁ።
[19] ነገር ግን የጌታችን ወንድም ያዕቆብን እንጂ ከሐዋርያት ሌላ አላየሁም።
[20] ስለምጽፍላችሁም ነገር እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት ሐሰት አልናገርም።
[21] ከዚህም በኋላ ወደ ሶርያና ወደ ቂልቅያ አውራጃ መጣሁ።
[22] በክርስቶስም ያሉት የይሁዳ ሀገር ማኅበረ ክርስቲያን ፊቴን አያውቁም ነበር።
[23] ነገር ግን “ቀድሞ ምእመናንን ያሳድድ የነበረው እርሱ በፊት ያጠፋው የነበረውን የሃይማኖት ትምህርት ዛሬ ይሰብካል ” ሲባል ወሬዬን ይሰሙ ነበር።
[24] ስለ እኔም እግዚአብሔርን ያመሰግኑት ነበር።