Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:13

[1] በእግዚአብሔር ፈቃድ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነ ከጳውሎስ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመኑ በኤፌሶን ላሉ ቅዱሳን፥

[2] ከአባታችን ከእግዚአብሔር፥ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስም ሰላምና ጸጋ ለእናንተ ይሁን።

[3] በክርስቶስ ኢየሱስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይመስገን።

[4] ዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳን፥ ንጹሓንና ያለ ነውር በፍቅር ያደርገን ዘንድ ለእርሱ መረጠን።

[5] በኢየሱስ ክርስቶስም እንደ ውድ ፈቃዱ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን።

[6] በሚወደው ልጁ የሰጠን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ።

[7] በእርሱም እንደ ቸርነቱ ብዛት በደሙ ድኅነትን አገኘን፤ ኀጢአታችንም ተሰረየልን።

[8] ይኸውም በፍጹም ጥበብና ምክር ለእኛ አብዝቶ ያደረገው ነው።

[9] እንደ ወደደም በእርሱ የወሰነውን፥ የፈቃዱን ምሥጢር ገለጠልን።

[10] የሚደርስበትንም ጊዜውን ወሰነ፤ በሰማይና በምድር ያለውም ሁሉ ይታደስ ዘንድ ክርስቶስን በሁሉ ላይ አላቀው።

[11] እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ እንደ እርሱ አሳብ አስቀድመን የተወሰን በእርሱ ርስትን ተቀበልን።

[12] ይኸውም አስቀድመን በክርስቶስ ኢየሱስ ተስፋ ያደረግን እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ነው።

[13] እናንተም ልትድኑበት የተማራችሁትን የእውነት ቃል ሰምታችሁና አምናችሁ፤ ተስፋ ባደረገላችሁ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ።

[14] ይኸውም ለጌትነቱ ክብር የርስታችን መያዣ፥ የሕይወታችንም ቤዛነት ነው።

[15] ስለዚህም እኔ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመናችሁን፥ ቅዱሳንንም ሁሉ መውደዳችሁን ሰምቼ፥

[16] ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ማመስገንንና በጸሎቴም እናንተን ማሰብን አላቌረጥሁም።

[17] ይኸውም የክብር ባለቤት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባቱ እግዚአብሔር የጥበብን መንፈስ ይሰጣችሁ ዘንድ፥ ዕውቀቱንም ይገልጽላችሁ ዘንድ፥

[18] ዐይነ ልቡናችሁንም ያበራላችሁ ዘንድ፥ የተጠራችሁበት ተስፋም ምን እንደ ሆነ፥ በቅዱሳንም የርስቱ ክብር ባለጸግነት ምን እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ፥

[19] በክርስቶስ እንደ አደረገው እንደ ከሃሊነቱ ታላቅነት በምናምን በእኛ ላይ የሚያደርገው የከሃሊነቱ ጽናት ብዛት ምን እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ ነው።

[20] ከሙታን ለይቶ ባስነሣው፥ በሰማይም በቀኙ ባስቀመጠው፥

[21] ከመላእክት ሁሉ በላይ ከመኳንንትና ከኀይላት፥ ከአጋእዝትና ከሚጠራውም ስም ሁሉ በላይ፥ በዚህ ዓለም ብቻ አይደለም፤ በሚመጣውም ዓለም እንጂ።

[22] ሁሉንም ከእግሩ በታች አድርጎ አስገዛለት፤ ከሁሉ በላይ የሆነ እርሱን ለቤተ ክርስቲያን ራስ አደረገው።

[23] ይህችውም አካሉ ናት፤ የሁሉም ፍጻሜው እርሱ ነው፤ ሁሉንም በሁሉ ይፈጽማል።

ወደ ኤፌሶን ሰዎች። — Chapters