[1] ልጆች ሆይ፥ ለወላጆቻችሁ በጌታችን ታዘዙ፤ ይህ የሚገባ ነውና።
[2] በሕግም ተስፋ ያለው የመጀመሪያው ትእዛዝ ይህ ነው ፥ “አባትህንና እናትህን አክብር፤
[3] መልካም ይሆንልህ ዘንድ፥ በምድር ላይም ዕድሜህ ይረዝም ዘንድ።”
[4] እናንተም አባቶች ሆይ፥ ልጆቻችሁን በእግዚአብሔር ተግሣጽና ምክር አሳድጉአቸው እንጂ አታስቈጡአቸው።
[5] አገልጋዮችም በሥጋችሁ ለሚገዙአችሁ ጌቶቻችሁ በፍርሀትና በመደንገጥ፥ በሰፊ ልብም ለክርስቶስ እንደምትገዙ ታዘዙ።
[6] የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሮች እንጂ ለሰው ደስ እንደሚያሰኝ ለታይታ አይደለም።
[7] ለሰው ሳይሆን ለእግዚአብሔር እንደምትገዙ በፍጹም ሰውነታችሁ በፍቅርና በበጎ ፈቃድ ተገዙላቸው።
[8] ጌታም ቢሆን፥ አገልጋይም ቢሆን መልካም ያደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ እንደሚያገኝ ታውቃላችሁና።
[9] እናንተም ጌቶች ሆይ፥ ቐጣችሁን እያበረዳችሁ፥ በደላቸውንም ይቅር እያላችሁ፥ ትክክለኛውን አድርጉላቸው፤ ፊት አይቶ የማያዳላ ጌታ በእነርሱና በእናንተ ላይ በሰማይ እንደ አለ ታውቃላችሁና።
[10] እንግዲህስ ወዲህ በእግዚአብሔርና በኀይሉ ጽናት በርቱ።
[11] የሰይጣንን ተንኰል መቌቌም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ጋሻ ልበሱ።
[12] ሰልፋችሁ ፥ ከጨለማ ገዦች ጋርና ከሰማይ በታች ካሉ ከክፉዎች አጋንንት ጋር ነው እንጂ ከሥጋዊና ከደማዊ ጋር አይደለምና።
[13] ስለዚህም በክፉ ቀን መቃወም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ጋሻ ያዙ፤ እንድትጸኑም በሁሉ የተዘጋጃችሁ ሁኑ።
[14] እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ ቁሙ፤ የጽድቅንም ጥሩር ልበሱ።
[15] የሰላም ወንጌል ኀይልንም ተጫምታችሁ ቁሙ።
[16] ከዚህም ሁሉ ጋር የሚንበለበሉ የክፉን ፍላፃዎች ሁሉ ማጥፋት እንድትችሉ የእምነትን ጋሻ አንሡ።
[17] የመዳንንም የራስ ቐር በራሳችሁ ላይ ጫኑ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ሰይፍ ያዙ፤ ይኸውም የእግዚአብሔር ቃል ነው።
[18] በጸሎትና በምልጃ ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ ከዚህም ጋር ስለ ቅዱሳን ሁሉ ለመጸለይ ሁልጊዜ ትጉ፤
[19] ለእኔም ፥ ቃልን እንዲሰጠኝ፥ አፌንም ከፍቼ የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንድናገር ጸልዩልኝ።
[20] ስለ ወንጌልም በእስራት መልእክተኛ የሆንሁ ፥ መናገር እንደሚገባኝ ስለ እርሱ በግልጥ እናገር ዘንድ ጸልዩ።
[21] እናንተም ዜናዬን እንድታውቁ የምንወደው ወንድማችን የታመነ የእግዚአብሔር አገልጋይ ቲኪቆስ የምሠራውን ሁሉ ያስረዳችኋል።
[22] ዜናዬን ታውቁ ዘንድ፥ ልባችሁም ይጽናና ዘንድ፥ ስለዚህ ወደ እናንተ ላክሁት።
[23] ከአባታችን ከእግዚአብሔር አብ፥ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስም ከእምነት ጋር ሰላምና ፍቅር ለወንድሞቻችን ይሁን።
[24] ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለ መጥፋት ከሚወዱት ሁሉ ጋር ጸጋ ይሁን። አሜን። በሮሜ ተጽፋ በቲኪቆስ እጅ ወደ ኤፌሶን ሰዎች የተላከች መልእክት ተፈጸመች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሜን።