Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 4:31

[1] ከኢየሱስ ክርስቶስ ባርያዎች ከጳውሎስና ከጢሞቴዎስ፥ በፊልጵስዩስ ለሚኖሩ፤ ከቀሳውስትና ከዲያቆናት ጋር በኢየሱስ ክርስቶስ ላሉ ቅዱሳን ሁሉ፤

[2] ከአባታችን ከእግዚአብሔር፥ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስም ሰላምና ጸጋ ለእናንተ ይሁን።

[3] እናንተን በማስብበት ጊዜ ሁሉ ዘወትር አምላኬን አመሰግነዋለሁ።

[4] ስለ እናንተም ሁልጊዜ እጸልያለሁ፤ የደስታ ጸሎትም አደርጋለሁ።

[5] ከመጀመሪያዪቱ ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ በወንጌል ትምህርት ከእኔ ጋር አንድ በመሆናችሁ፥

[6] እርሱ የጀመረላችሁን በጎውን ሥራ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከሚመጣበት ቀን ድረስ እርሱ እንደሚፈጽምላችሁ አምናለሁ።

[7] ስለ እናንተ ይህን ላስብ ይገባኛል፤ በምታሰርበትና በምከራከርበት፥ ወንጌልንም በማስተምርበት ጊዜ ከእኔ ጋራ በጸጋ ስለ ተባበራችሁ በልቤ ውስጥ ናችሁና።

[8] በክርስቶስ ፍቅር ሁላችሁን እንደምወዳችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነው።

[9] ስለዚህም በአእምሮና በልብ ጥበብ ሁሉ ፍቅራችሁ እንዲበዛ፥ እንዲጨምርም እጸልያለሁ፤

[10] የሚሻለውን ሥራ እንድትመረምሩና እንድትፈትኑ፥ ክርስቶስ በሚመጣበት ቀን ያለ ዕንቅፋት ቅዱሳን ትሆኑ ዘንድ ፥

[11] ለእግዚአብሔር ምስጋናና ክብርም በኢየሱስ ክርስቶስ የጽድቅን ፍሬ ትሞሉ ዘንድ እጸልያለሁ፤

[12] ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህ የደረሰብኝ በእውነት ወንጌልን ለማስፋፋት እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ እወድዳለሁ።

[13] ስለ ክርስቶስ ስም መታሰሬም በአደባባዩ ሁሉና በሰው ሁሉ ዘንድ ታውቆአል።

[14] ከወንድሞቻችንም ብዙዎቹ በእስራቴ ምክንያት በጌታ ታመኑ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ያለ ፍርሀት ጨክነው ያስተምሩ ዘንድ እጅግ ተደፋፈሩ።

[15] ከእነርሱ አንዳንዶች በቅናታቸውና በክርክራቸው፥ ሌሎችም በበጎ ፈቃድ ስለ ክርስቶስ ሊሰብኩና ሊያስተምሩ የወደዱ አሉ።

[16] በፍቅር የሚያስተምሩም አሉ፤ ወንጌልን ለማስተማር እንደ ተሾምሁ ያውቃሉና።

[17] በኵuራት ስለ ክርስቶስ የሚያስተምሩ ግን፥ ይህን አድርገው በእስራቴ ላይ መከራ ሊጨምሩብኝ መስሎአቸው ነው እንጂ በእውነት አይደለም፤ በቅንነትም አይደለም።

[18] ነገር ግን ምን አለ? በየምክንያቱ በእውነትም ቢሆን፥ በሐሰትም ቢሆን፥ ስለ ክርስቶስ ይናገራሉ፤ ሰውንም ሁሉ ወደ እርሱ ይጠራሉ፤ በዚህም ደስ ብሎኛል፤ ወደፊትም ደስ ይለኛል።

[19] እኔም ይህቺ ሥራ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ወደ ሕይወት እንደምታደርሰኝ አውቃለሁ።

[20] በምንም እንደማላፍር ተስፋ እንደ አደረግሁና እንደታመንሁ እንደ ወትሮው በልብ ደስታ በግልጥነት፥ አሁንም የክርስቶስ ክብር በሕይወቴም ቢሆን፥ በሞቴም ቢሆን በሰውነቴ ይገለጣል።

[21] እኔ በሕይወት ብኖርም ክርስቶስን ለማገልገል ነው፤ ብሞትም ዋጋ አለኝ።

[22] ነገር ግን በሥጋ መኖር ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢሆንም ምን እንደምመርጥ አላውቅም።

[23] በእነዚህ በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ እኔስ ከዚህ ዓለም ልለይ፥ በከክርስቶስም ዘንድ ልኖር እወዳለሁ፤ ይልቁንም ለእኔ ይህ ይሻለኛል፤ ይበልጥብኛልም።

[24] ደግሞም ስለ እናንተ በሕይወተ ሥጋ ብኖር ይሻላል።

[25] ይህንም ዐውቄ ለማደጋችሁና በሃይማኖትም ለምታገኙት ደስታ እንደምኖር አምናለሁ።

[26] ዳግመኛ ወደ እናንተ በመምጣቴ በእኔ ምክንያት በኢየሱስ ክርስቶስ የምታገኙት ክብር ይበዛላችሁ ዘንድ።

[27] ነገር ግን ምናልባት የመጣሁ እንደ ሆነ፥ ሳልኖርም ቢሆን በወንጌል ሃይማኖት እየተጋደላችሁ በአንድ መንፈስና በአንድ አካል ጸንታችሁ እንደምትኖሩ አይና እሰማ ዘንድ ሥራችሁ ለክርስቶስ ትምህርት እንደሚገባ ይሁን።

[28] የእነርሱ ጥፋት፥ የእናንተም ሕይወት ይታወቅ ዘንድ የሚቃወሙን ሰዎች በማናቸውም አያስደንግጧችሁ።

[29] ይህንም ጸጋ እግዚአብሔር ሰጥቶአችኋል፤ ነገር ግን ስለ እርሱ መከራ ልትቀበሉም ነው እንጂ ልታምኑበት ብቻ አይደለም።

[30] እንዲሁም እኔን እንዳያችሁኝ፥ የእኔንም ነገር እንደ ሰማችሁ ምንጊዜም ተጋደሉ።

ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች። — Chapters