Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 4:00

[1] እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን ምሰሉ።

[2] ክርስቶስ እንደ ወደዳችሁ፥ ራሱንም ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ የሚሆን መሥዋዕትና ቐርባን አድርጎ እንደ ሰጠላችሁ በፍቅር ተመላለሱ።

[3] ነገር ግን ለቅዱሳን እንደሚገባቸው፥ ዝሙትና ርኵuሰት ሁሉ ወይም ቅሚያ አይሰማባችሁ።

[4] የሚያሳፍር ነገርም፥ የስንፍና ነገርም፥ ወይም የማይገባ የዋዛ ነገር በእናንተ ዘንድ አይሁን፤ ማመስገን ይሁን እንጂ።

[5] ሴሰኛ፥ ወይም ኀጢአተኛ፥ ወይም ቀማኛ፥ ወይም ጣዖትን የሚያመልክ ሁሉ በእግዚአብሔር ልጅ በክርስቶስ መንግሥት ዕድል ፋንታ እንደሌለው ይህን ዕወቁ።

[6] በከንቱ ነገርም የሚያስታችሁ አይኑር፤ በእርሱ ምክንያት በከሓዲዎች ልጆች ላይ የእግዚአብሔር መዓት ይመጣልና።

[7] እንግዲህ አትምሰሉአቸው።

[8] ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና፥ ዛሬ ግን በጌታችን ብርሃን ሆናችኋል። እንግዲህስ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ።

[9] የብርሃን ፍሬው በጎ ሥራና እውነት፥ ቅንነትም ሁሉ ነውና።

[10] እግዚአብሔርንም ደስ የሚያሰኘውን መርምሩ።

[11] የሥራ ፍሬ ከሌላቸው፥ ሁለንተናቸውም ጨለማ ከሆነ ሰዎች ጋር አትተባበሩ፤ ገሥጹአቸው እንጂ።

[12] በስውር የሚሠሩት ሥራ ለመናገር የሚያሳፍር ነውና።

[13] ነገር ግን በብርሃን የተገለጠ ሁሉ ይታወቃል፤ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና።

[14] “የተኛህ ንቃ ከሙታንም ተለይተህ ተነሥ፤ ክርስቶስም ያበራልሃል ” ብሎአልና።

[15] እንግዲህ እንደ ዐዋቂዎች እንጂ እንደ አላዋቂዎች ሳይሆን እንዴት እንደምትመላለሱ በጥንቃቄ ዕወቁ።

[16] ቀኖች ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁት።

[17] ስለዚህም ሰነፎች አትሁኑ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ አስተውሉ እንጂ።

[18] መዳራት ነውና ወይን በመጠጣት አትስከሩ፤ መንፈስ ቅዱስን ተመሉ እንጂ።

[19] መዝሙርንና ምስጋናን፥ የተቀደሰ ማሕሌትንም አንብቡ፤ በልባችሁም ለእግዚአብሔር ተቀኙ፤ ዘምሩም።

[20] ዘወትርም ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ለእግዚአብሔር አብ ምስጋና አቅርቡ።

[21] እግዚአብሔርን በመፍራት ለባልንጀሮቻችሁ ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ።

[22] ሴቶችም ለጌታችን እንደሚታዘዙ ለባሎቻቸው ይታዘዙ።

[23] ክርስቶስ አካሉ ለሆነችው ቤተ ክርስቲያን ራስዋ አዳኝዋም እንደ ሆነ ወንድ ለሴት ራስዋ ነውና።

[24] ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትታዘዝ፥ እንዲሁም ሴቶች ለባሎቻቸው በሁሉ ይታዘዙ።

[25] ወንዶችም ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት፥ ራሱንም ስለ እርስዋ ቤዛ አድርጎ እንደ ሰጠላት ሚስቶቻቸውን ይውደዱ።

[26] በውኃ ጥምቀትና በቃሉ ይቀድሳትና ያነጻት ዘንድ፥

[27] የነጻችና የተቀደሰች ትሆን ዘንድ እንጂ በላይዋ እድፈት ወይም ርኵuሰት እንዳያገኝባት፥ ቤተ ክርስቲያኑን ለእርሱ የከበረች ያደርጋት ዘንድ፤

[28] እንዲሁም ወንዶች ሚስቶቻቸውን እንደ ራሳቸው አድርገው ይውደዱ፤ ሚስቱንም የወደደ ራሱን ወደደ።

[29] ከቶ ሥጋውን መጥላት የሚቻለው የለም፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ መገባት መግቡ፤ ጠብቁም።

[30] እኛ የአካሉ ሕዋሳት ነንና።

[31] “ስለዚህም ወንድ አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር አንድ ይሆናል፤ ሁለቱም አንድ አካል ይሆናሉ።”

[32] ይህም ምሥጢር ታላቅ ነው፤ እኔም ይህንኑ ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያኑ እናገረዋለሁ።

[33] እንግዲያስ እናንተም ሁላችሁ እንዲሁ ሚስቶቻችሁን እንደ ራሳችሁ ውደዱ፥ ሴትም ባልዋን ትፍራው።

ወደ ኤፌሶን ሰዎች። — Chapters