[1] ወንድሞቻችን ሆይ፥ ለተጠራሁላት አጠራር በሚገባ ትኖሩ ዘንድ በክርስቶስ እስረኛ የሆንሁ እኔ ጳውሎስ እማልዳችኋለሁ።
[2] በፍጹም የዋህነት ራሳችሁን ዝቅ አድርጋችሁ እየታገሣችሁ፥ ለወንድሞቻችሁም እሺ እያላችሁ፥ በፍቅር እየተጋችሁና እየተባበራችሁ፥
[3] በአንድ መንፈስና በሰላም ማሰሪያነት እየተጠበቃችሁ፥
[4] ለአንዱ ተስፋችሁ እንደ መጠራታችሁ መጠን፥ አንድ አካልና አንድ መንፈስ ትሆኑ ዘንድ እማልዳችኋለሁ።
[5] ጌታ አንድ ነው፤ ሃይማኖትም አንዲት ናት፤ ጥምቀትም አንዲት ናት።
[6] በሁሉ ሙሉ የሚሆን ሁሉም ከእርሱ የተገኘ ከሁሉም በላይ ያለ የሁሉ አባት እግዚአብሔር አንድ ነው።
[7] ከእኛ ለእያንዳንዱ በክርስቶስ ስጦታ መጠን ጸጋው ተሰጥቶናል።
[8] “ምርኮን ማርከህ ወደ ሰማይ ወጣህ፤ ጸጋህንም ለሰው ልጅ ሰጠህ ” ይላልና።
[9] ከምድር በታች ካልወረደ መውጣቱ ምንድን ነው?
[10] የወረደው እርሱ ነው፤ ሁሉንም ይመላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ እርሱ ነው።
[11] እርሱም ጸጋን ሰጠ፤ ከቤተ ሰቦቹም ሐዋርያትን፥ ከእነርሱም ነቢያትንና የወንጌል ሰባኪዎችን፥ ጠባቂዎችንና መምህራንን ሾመ።
[12] ቅዱሳን ለአገልግሎቱ ሥራና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ እንዲጸኑ፤
[13] ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ አንድ እስክንሆን ድረስ በክርስቶስ ምልዐት መጠን፥ አካለ መጠን እንደ አደረሰ እንደ አንድ ሙሉ ሰው እስክንሆን ድረስ፥
[14] እንግዲህ በሽንገላቸው ያስቱ ዘንድ በሚተናኰሉ ሰዎች ተንኰል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ ወዲያና ወዲህ እየተፍገመገምንና እየተንሳፈፍን ሕፃናት አንሁን።
[15] ነገር ግን በፍቅር እውነተኟች እንሆን ዘንድ ራስ ወደ ሆነው ወደ እርሱ ወደ ክርስቶስ እንደግ።
[16] ከእርሱ የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ በተሰጠው በሥር ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል።
[17] እንግዲህ በልባቸው ከንቱ አሳብ እንደሚኖሩ እንደ አሕዛብ እንዳትኖሩ ይህን እላለሁ፤ በእግዚአብሔርም እመሰክራለሁ።
[18] ልቡናቸው የተጨፈነ ነው፤ በስንፍናቸውና በድንቐርናቸው እግዚአብሔር ከሚሰጣቸው ሕይወት የተለዩ ናቸው።
[19] ተስፋ የቈረጡ ናቸው፤ ራሳቸውንም ለጕuስቐልና፥ ለርኵuሰትና ለመዳራት አሳልፈው ሰጡ።
[20] እናንተ ግን ክርስቶስን የተማራችሁት እንደዚህ አይደለም።
[21] በርግጥ ከሰማችሁት፥ እውነት በኢየሱስ ክርስቶስ ነውና እውነትን በእርሱ ዘንድ ትማራላችሁ፤
[22] የቀድሞ ጠባያችሁን ከእናንተ አርቁ፤ ይህንም ስሕተት በሚያመጣው ምኟት ስለሚጠፋው ስለ አሮጌው ሰውነት እላለሁ።
[23] የልቡናችሁን ዕውቀት አድሱ።
[24] እግዚአብሔርም በእውነት፥ በቅንነትና በንጽሕና ያደሰውን አዲሱን ሰውነት ልበሱት።
[25] ስለዚህም ሐሰትን ተዉአት፤ ሁላችሁም ከወንድሞቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ፤ እኛ አንድ አካል ነንና።
[26] ተቈጡ፤ አትበድሉም፤ ፀሐይ ሳይጠልቅም ቐጣችሁን አብርዱ።
[27] ለሰይጣንም መንገድን አትስጡት።
[28] የሚሰርቅም እንግዲህ አይስረቅ፤ ነገር ግን ድሃውን ይረዳ ዘንድ በእጆቹ መልካም እየሠራ ይድከም።
[29] የሚሰሙአችሁ ሞገስን ያገኙ ዘንድ፥ ግዳጃችሁ እንዲፈጸም መልካም ነገር እንጂ ክፉ ነገር ሁሉ ከአፋችሁ አይውጣ።
[30] በዳናችሁ ጊዜ የታተማችሁበትን የእግዚአብሔርን ቅዱስ መንፈስ አታሳዝኑት።
[31] መራራነትንና ቐጣን፥ ብስጭትንና ርግማንን፥ ጥፋትንና ስድብን ሁሉ ከክፉ ነገር ሁሉ ጋር ከእናንተ አርቁ።
[32] እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፤ እግዚአብሔርም በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ።