Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 2:41

[1] ስለዚህ አሕዛብ ሆይ ስለ እናንተ እኔ ጳውሎስ የክርስቶስ እስረኛው ነኝ።

[2] ስለ እናንተ የሰጠኝን የእግዚአብሔርን የጸጋውን ስጦታ ሰምታችኋል።

[3] አስቀድሞ በጥቂቱ እንደ ጻፍሁላችሁ ይህን ምሥጢር ገልጦ አሳይቶኛልና።

[4] ይህንም በምታነቡበት ጊዜ፥ የክርስቶስን ምሥጢር ማስተዋሌን ለማወቅ ትችላላችሁ።

[5] በሌላ ዘመን ለሰው ልጆች ያልተገለጠ ዛሬ ለቅዱሳን ሐዋርያቱና ለነቢያቱ በመንፈስ ቅዱስ እንደ ተገለጠ፥

[6] አሕዛብን ወራሾቹና አካሉ ያደርጋቸው ዘንድ፥ በወንጌልም ትምህርት በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ተስፋ አንድ ይሆኑ ዘንድ።

[7] በኀይሉ አጋዥነት እንደ ሰጠኝ እንደ ጸጋው ስጦታ መጠን እኔ መልእክተኛና አዋጅ ነጋሪ የሆንሁለት፥

[8] ከቅዱሳን ሁሉ ለማንስ ለእኔ የማይመረመረውን የክርስቶስን ባለጸግነት ለአሕዛብ አስተምር ዘንድ ይህን ጸጋ ሰጠኝ።

[9] ሁሉን በፈጠረ በእግዚአብሔር ከዘለዓለም የተሰወረ የዚህ ምሥጢር ሥርዐትንም ለሁሉ እገልጥ ዘንድ፤

[10] ብዙ ልዩ ልዩ የሆነች የእግዚአብሔር ጥበብ አሁን በቤተ ክርስቲያን በኩል በሰማያዊ ስፍራ ውስጥ ላሉት አለቆችና ሥልጣናት ትታወቅ ዘንድ፤

[11] ዓለም ሳይፈጠር የወሰናት፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም የፈጸማት፥

[12] እኛ ጸጋንና ባለሟልነትን ያገኘንበት፥ በሃይማኖት ወደሚገኘው ተስፋም ያደረሰበት፤

[13] ስለዚህም ስለ እናንተ ለክብራችሁ የምታገኘኝን መከራዬን ቸል እንዳይላት እግዚአብሔርን እማልደዋለሁ።

[14] ስለዚህም በልቡናዬ ተንበርክኬ ለአብ እሰግዳለሁ።

[15] በሰማይና በምድር ያሉ ነገዶች ሁሉ ለሚጠሩት ለእርሱ፤

[16] እንደ ጌትነቱ ምላት ይሰጣችሁ ዘንድ፥ በመንፈስ ቅዱስም ኀይል ያጸናችሁ ዘንድ።

[17] በልባችሁ ውስጥ በፍቅር ሥር መሠረታችሁ የጸና ሲሆን ክርስቶስ በሃይማኖት በሰው ውስጥ ያድራልና።

[18] ስፋቱና ርዝመቱ፥ ምጥቀቱና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደ ሆነ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ለማስተዋል ትችሉ ዘንድ፥

[19] የክርስቶስን ፍቅር ለመረዳት፥ በእግዚአብሔር ፍጹምነት በሁሉ ፍጹማን ትሆኑ ዘንድ።

[20] በከሃሊነቱ እንደ ረዳን መጠን፥ የምናስበውንና የምንለምነውን ሁሉ ትሠሩ ዘንድ፥ ታበዙም ዘንድ ሊያጸናችሁ ለሚችል፥

[21] ለእርሱ በቤተ ክርስቲያን በኢየሱስ ክርስቶስ፥ በትውልድ ሁሉ ምስጋና ይሁን ለዘለዓለሙ አሜን።

ወደ ኤፌሶን ሰዎች። — Chapters