[1] የእግዚአብሔር ስምና ትምህርቱ እንዳይነቀፉ ከቀንበር በታች ያሉ አገልጋዮች ሁሉ ለጌቶቻቸው ክብር ሁሉ እንደሚገባ ይቐጠሩ።
[2] ያመኑ ጌቶች ያሉአቸውም ቢኖሩ አይናቌቸው፤ እነርሱ ወንድሞቻቸው ናቸውና፤ ደግሞም አብዝተው ያገልግሉአቸው፤ በመልካም ሥራቸው ተቀብለው የሚረዱአቸው የታመኑና የተወደዱ ናቸውና፤ እንደዚህ አስተምርና ምከር
[3] ሌላ ትምህርት የሚያስተምር፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ወደ ሆነው ወደ ሕይወት ነገር ትምህርትና ወደ መልካም አምልኮ ትምህርት የማይመለስ ቢኖር፥
[4] እንዲህ ያለው ሰው ይታበያል፤ አንዳችም አያውቅም፤ ነገር ግን ምርመራንና በቃል መዋጋትን እንደ በሽተኛ ይናፍቃል፤ ከእነዚህም ቅናትና ክርክር፥ ስድብም፥ ክፉ አሳብም፥ እርስ በርስ መናደድም ይወጣሉ።
[5] አእምሮአቸው የጠፋባቸውና ከዕውነት የራቁ፥ መልካም አምልኮን መናገጃ የሚያደርጉ አሉ፤ ከእነዚህም ራቅ።
[6] በቃኝ ከማለት ጋር እግዚአብሔርን ማምለክ ታላቅ ረብ ነው።
[7] ወደ ዓለም ያመጣነው የለንምና፤ ከእርሱም ልንወስደው የምንችል የለምና።
[8] ምግባችንንና ልብሳችንን ካገኘን ይበቃናል።
[9] ባለጸጋ ሊሆኑ የሚወዱ ግን በጥፋትና በመፍረስ፥ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ፥ በሚጎዳም በብዙ ምኟትና በፈተና፥ በወጥመድም ይወድቃሉ።
[10] ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ ይህንም በመመኘት ተሳስተው ሃይማኖታቸውን የለወጡ ብዙዎች ናቸውና፥ ለራሳቸውም ብዙ መቅሠፍትን ሽተዋልና።
[11] የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ አንተ ግን ከዚህ ሁሉ ራቅ፤ ጽድቅንና መልካም አምልኮን፥ ሃይማኖትንና ፍቅርን፥ ትዕግሥትንና የዋህነትንም ተከታተል።
[12] የተጠራህለትንና በብዙ ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘለዓለምን ሕይወት ለመቀበል መልካሙን የሃይማኖት ገድል ተጋደል።
[13] ሁሉን በሕይወት በሚጠብቅ በእግዚአብሔር ፊት፥ በጴንጤናዊውም በጲላጦስ ፊት መልካሙን መታመን በመሰከረ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት አዝዝሃለሁ።
[14] ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪገለጥ ድረስ፥ ያለ ነውርና ያለ ሐሜት ሆነህ ይህን ትእዛዝ ጠብቅ።
[15] ይህንም ብፁዕና ብቻውን ኀያል የሆነ፥ የነገሥታት ንጉሥ፥ የጌቶች ጌታ በጊዜው ይገልጠዋል።
[16] እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ አንድ ሰው እንኳ አላየውም፤ ሊያየውም አይቻለውም፤ ለእርሱ ክብርና የዘለዓለም ኀይል ይሁን፤ አሜን።
[17] የዚህን ዓለም ባለጸጎችም እንዳይታበዩ፥ ደስ እንዲለንም በባለጸግነቱ ብዛት ሁሉን አብዝቶ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለጸግነታቸው እንዳይታመኑ እዘዛቸው።
[18] በጎ ሥራን እንዲሠሩ፥ በበጎ ሥራም ባለጸጎች እንዲሆኑ፥ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው።
[19] በሚመጣውም ዓለም ዕውነተኛውን ሕይወት ለማግኘት ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እንዲሰበስቡ ምከራቸው።
[20] ጢሞቴዎስ ሆይ፥ የተሰጠህን አደራ ጠብቅ፤ ከንቱ ነገር የሚያመጡትንና ዕውነትን በሐሰት የሚያርቁ ርኩሳንንም ተለያቸው።
[21] እነርሱ በሃይማኖት ከሚገኘው ተስፋ ወጥተዋልና፤ ጸጋ ከአንተ ጋር ይሁን፤ አሜን። በሎዶቅያ ተጽፎ በቲቶ እጅ ወደ ጢሞቴዎስ የተላከ መጀመሪያዉ መልእክት ተፈጸመ። አሜን።