Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:15

[1] በመድኀኒታችን በእግዚአብሔር፥ በተስፋችን በኢየሱስ ክርስቶስም ትእዛዝ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሚሆን ከጳውሎስ፥

[2] በሃይማኖት ለምወድህ ልጄ ለጢሞቴዎስ፥ የአባታችን የእግዚአብሔርና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም፥ ጸጋና ምሕረት ለአንተ ይሁን።

[3] ወደ መቄዶንያ በሄድሁ ጊዜ በኤፌሶን እንድትቀመጥ ለምኜህ ነበር። ትገሥጻቸው ዘንድ ሌላ ትምህርት እንዳያመጡ፥

[4] ፈጥረው የሚናገሩትንም ተረትና ጨዋታ እንዳያመጡ፤ እነርሱም ሊያስቱ ክርክርን ያመጣሉ፤ በሃይማኖት ያለውንም የእግዚአብሔርን ሕግ ይተዋሉ።

[5] የትእዛዝ ፍጻሜ ግን በንጹሕ ልብና በመልካም ጠባይ፥ ጥርጥር በሌለበትም እምነት መፋቀር ነው።

[6] ከዚህ ወጥተው ወደ ከንቱ ነገር የተመለሱ አሉና።

[7] የሕግ መምህራን ሊሆኑ ሲወዱ ራሳቸው የሚናገሩትንና የሚያስረዱትን አያውቁም።

[8] ኦሪት እንደሚገባ ለሚሠራበት መልካም እንደ ሆነ እናውቃለን።

[9] ሕግ የሚሠራ ለጻድቃን እንዳይደለ ይህን እናውቃለን፤ ለኀጢአተኟችና ለከዳተኟች፥ ኀጢአትን ለሚያዘወትሩና ከእውነት ለወጡ፥ ለርኵuሳን፥ አባትና እናታቸውን ለሚገድሉ ነፍሰ ገዳዮችም፥

[10] ለሴሰኟችና ለአመንዝራዎች፥ ሰውን ለሚሰርቁ፥ ሐሰት ለሚናገሩና በሐሰት ለሚምሉም ነው እንጂ።

[11] የቡሩክ እግዚአብሔርንም ክብር የሚገልጥ ለእኔ አደራ የተሰጠኝ የወንጌልን የሕይወት ትምህርት ለሚቃወሙም ነው እንጂ።

[12] ያጸናኝን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አመሰግነዋለሁ፤ ለመልእክቱ ሾሞ ታማኝ አድርጎኛልና።

[13] እኔ ቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ፥ ተቃዋሚም ስሆን፥ ሳላውቅ ባለ ማመን ስለ አደረግሁት ይቅር አለኝ።

[14] የእግዚአብሔር ጸጋው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከማመንና ከመውደድ ጋር በእኔ ላይ በዛ።

[15] ነገሩ የታመነ ነው፤ ሁሉም ሊቀበሉት የሚገባ ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ መጀመሪያቸው የሆንሁ ኃጥኣንን ሊያድን ወደ ዓለም መጥቶአልና።

[16] ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ በእኔ ላይ የትዕግሥቱን ብዛት ይገልጥ ዘንድ፥ የዘለዓለም ሕይወትን ለማግኘት በእርሱ ለሚያምኑም ምሳሌ እሆናቸው ዘንድ ይቅር አለኝ።

[17] ብቻውን አምላክ ለሚሆን ለማይሞተው፥ ለማይታየውም ለዘለዓለም ንጉሥ ምስጋናና ክብር እስከ ዘለዓለም ድረስ ይሁን፤ አሜን።

[18] ልጄ ጢሞቴዎስ ሆይ፥ በአንተ ላይ እንደ ተነገረው ትንቢት፥ መልካም ገድልን እንድትጋደል ይህን ትእዛዝ አደራ እልሃለሁ።

[19] ሃይማኖትና መልካም ሕሊና ይኑሩህ፤ ከሃይማኖት የወጡና የጠፉ አሉና።

[20] ከእነዚህም ደግሞ እንዲቀጡና ስድብን እንዳይማሩ ለሰይጣን አሳልፌ የሰጠኋቸው ሄሜኔዎስና እለእስክንድሮስ ናቸው።

ወደ ጢሞቴዎስ። 1 — Chapters