[1] አሁንም ወንድሞቻችን ሆይ፥ በእናንተ ዘንድ እንደ ሆነው የእግዚአብሔር ቃል እንዲፋጠንና እንዲከብር ጸልዩልን።
[2] ከክፉዎችና ከከሓዲዎች ሰዎችም እንድን ዘንድ ጸልዩልን፤ ሁሉ አማኝ አይደለምና።
[3] ነገር ግን የሚያጸናችሁና ከክፉ ሁሉ የሚጠብቃችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው።
[4] ያዘዝናችሁን እንድታደርጉ በእግዚአብሔር እንተማመናችኋለን፤ ታደርጉታላችሁም።
[5] ጌታችንም፥ ወደ እግዚአብሔር ፍቅር ወደ ክርስቶስም ትዕግሥት ልባችሁን ያቅና።
[6] ወንድሞቻችን ሆይ፥ በሠራንላቸው ሥርዐት ሳይሆን በተንኰል ከሚሄዱት ወንድሞች ሁሉ፥ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዝዛችኋለን።
[7] እኛን ልትመስሉ እንደሚገባችሁ፥ እኛም በእናንተ መካከል ያለ ሥራ እንዳልኖርን ራሳችሁ ታውቃላችሁ።
[8] በእናንተ ላይ እንዳንከብድባችሁ፥ ቀንና ሌሊት በድካምና በጥረት እየሠራን እንጂ የሌላውን እህል በከንቱ አልበላንም።
[9] ይህም እኛን ልትመስሉን ምሳሌ እንድንሆናችሁ ነው እንጂ ያለ ሥልጣን ስለ ሆንን አይደለም።
[10] በእናንተ ዘንድ በነበርን ጊዜም “ሊሠራ የማይወድ አይብላ ” ብለን አዝዘናችሁ ነበርና።
[11] በውስጣችሁ በስንፍና የሚኖሩ እንዳሉ ሰምተናል፤ የሚሠሩትም ሥራ የላቸውም፤ ደግሞም ዘዋሪዎች ናቸው።
[12] እንደ እነዚህ ያሉትንም በጸጥታ ሥራቸውን እየሠሩ የገዛ ምግባቸውን ይመገቡ ዘንድ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እናዝዛቸዋለን፤ እንመክራቸዋለንም።
[13] ወንሞቻችን ሆይ፥ እናንተ ግን ሁልጊዜ ሥራ መሥራትን ቸል አትበሉ።
[14] ለቃላችንና ለመልእክታችን የማይታዘዝ ቢኖር ይለይ፤ እንዲያፍርም አትጨመሩት።
[15] ነገር ግን ወንድማችሁ እንደ መሆኑ ምከሩት እንጂ፥ እንደ ጠላት አታድርጉት።
[16] የሰላም አምላክ እርሱ ሁልጊዜ በሥራው ሁሉ ሰላምን ይስጣችሁ፤ ጌታችንም ከሁላችሁ ጋር ይኑር።
[17] እኔ ጳውሎስ ይህን ሰላምታ በእጄ ጻፍሁ፤ በመልእክቶቼ ሁሉ ምልክቴ ይህ ነው፤ እንዲህ እጽፋለሁ።
[18] የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን። ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች የተላከ ሁለተኛዉ መልእክት ተፈጸመ፤ በሎዶቅያ ተጻፈ በቲኪቆስ እጅ ተላከ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሜን።