[1] ከጳውሎስ፥ ከስልዋኖስና ከጢሞቴዎስ በአባታችን በእግዚአብሔር፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላመኑ በተሰሎንቄ ላሉ ማኅበረ ክርስቲያን፤
[2] የአባታችን የእግዚአብሔር፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስም ሰላምና ጸጋ ለእናንተ ይሁን።
[3] ወንድሞቻችን ሆይ፥ እንደሚገባ ስለ እናንተ ዘወትር እግዚአብሔርን ልናመሰግነው ይገባል፤ ሃይማኖታችሁ አድጋለችና፥ ከባልንጀራችሁም ሁሉ ጋር ፍቅራችሁ በዝታለችና።
[4] ስለዚህ በምትታገሡበት በስደታችሁና በመከራችሁ ስለ ሃይማኖታችሁና ስለ ትዕግሥታችሁ በእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በእናንተ እንመካለን።
[5] እግዚአብሔር መከራ የምትቀበሉለትን መንግሥቱን ያድላችሁ ዘንድ ይህ የእግዚአብሔር የእውነተኛ ፍርዱ ምልክት ነው።
[6] መከራ የሚያጸኑባችሁ እነዚያ በእግዚአብሔር ዘንድ ፍዳቸውን ይቀበሉ ዘንድ ይገባል።
[7] ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኀይሉን ከሚገልጥባቸው መላክእቱ ጋር በሚመጣበት ጊዜ፥ መከራ ለምትቀበሉ ለእናንተ ከእኛ ጋር ዕረፍት ይገባችኋል።
[8] እግዚአብሔርን የማያውቁትን፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስንም ወንጌል የማይሰሙትን ይበቀላቸዋል።
[9] ከጌታችን ፊት፥ ከኀይሉም ክብር ርቀው የዘለዓለም ጥፋት ፍዳቸውን ያገኛሉ።
[10] በቅዱሳኑ ይከበር ዘንድ፥ በሚያምኑትም ይመሰገን ዘንድ በሚመጣ ጊዜ፥ በዚያች ቀን ለእናንተ የመሰከርነው ምስክርነታችን ይታመንልናልና።
[11] ስለዚህ እግዚአብሔር ለመጥራቱ የተገባችሁ ያደርጋችሁ ዘንድ፥ ይቅርታውንና በጎነቱን፥ የእምነትንም ሥራ በኀይል ይፈጽምላችሁ ዘንድ ዘወትር እንጸልያለን።
[12] እንደ አምላካችንና እንደ ጌታችን እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም በእናንተ ላይ ይከብር ዘንድ፥ እናንተም በእርሱ ትከብሩ ዘንድ እንጸልያለን።