Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:35

[1] ወንድሞቻችን ሆይ፥ ስለ ዘመኑና ስለ ወራቱ፥ ስለ ቀኑም፥ ልንጽፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤

[2] የጌታችን ቀን ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ እንዲሁ ትመጣ ዘንድ እናንተ ራሳችሁ በርግጥ ታውቃላችሁና።

[3] ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ ያንጊዜ ምጥ የፀነሰችን ሴት እንደሚይዛት፥ ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል፤ ማምለጥም አይቻላቸውም፤

[4] እናንተ ግን ወድሞቻችን ሆይ፥ ቀኑ እንደ ሌባ ይደርስባችሁ ዘንድ በጨለማ ውስጥ አይደላችሁም።

[5] ሁላችሁም የብርሃን ልጆች፥ የቀንም ልጆች ናችሁና፤ እኛ ከሌሊት፥ ወይም ከጨለማ አይደለንም።

[6] እንግዲህ እንንቃ፤ እንትጋ፤ እንወቅም እንጂ እንደ እነዚያ አናንቀላፋ።

[7] የሚያንቀላፉ በሌሊት ያንቀላፋሉና፤ የሚሰክሩም በሌሊት ይሰክራሉና።

[8] እኛ ግን የቀን ልጆች ስለሆን እንንቃ፤ የሃይማኖትንና የፍቅርን ጥሩር እንልበስ፤ ተስፋ ያለበት የመዳንን ራስ ቐርም እንቀዳጅ።

[9] እግዚአብሔር በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለሕይወትና ለደኅንነት እንጂ፥ ለጥፋት አላደረገንምና።

[10] የምንነቃ፥ ወይም የምናንቀላፋ ብንሆን፥ ሁላችን ከእርሱ ጋር በሕይወት እንኖር ዘንድ፥ ስለ እኛ ቤዛ ሆኖ ሞተ።

[11] አሁንም ስለዚህ እናንተ እንደምታደርጉ ወንድሞቻችሁን አጽናኑ። አንዱም አንዱም ወንድሙን ያንጸው።

[12] ወድሞቻችን ሆይ፥ በመካከላችሁ የሚደክሙትን፥ በጌታችን የሚቆሙላችሁንና የሚአስተምሩአችሁንም ዕወቌቸው ብለን እንማልዳችኋለን።

[13] እጅግ አክብሩአቸው፤ ስለ ሥራቸውም ውደዱአቸው፤ እርስ በርሳችሁም በሰላም ሁኑ።

[14] ወንድሞቻችን እንማልዳችኋለን፤ ያለ ሥርዐት የሚሄዱትንም ገሥጹአቸው፤ ያዘኑትንም አረጋጉአቸው፤ የደከሙትን አጽኑአቸው፤ ሁሉንም ታገሡ።

[15] በክፉ ፋንታ ክፉ እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ ነገር ግን ዘወትር እርስ በርሳችሁ ለሌላው መልካም ነገርን ትሠሩ ዘንድ ተሽቀዳደሙ።

[16] ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ።

[17] ያለማቌረጥም ጸልዩ።

[18] ስለ ሥራው ሁሉ እግዚአብሔርን አመስግኑት፤ ስለ እናንተ የእግዚአብሔር ፈቃዱ በኢየሱስ ክርስቶስ ይህ ነውና።

[19] መንፈስን አታጥፉ።

[20] ትንቢትንም አትናቁ።

[21] ሁሉን መርምሩ፤ መልካም የሆነውንም ያዙ።

[22] ከክፉ ሥራ ሁሉ ራቁ።

[23] የሰላም አምላክ እግዚአብሔር ፈጽሞ ይቀድሳችሁ፤ ነፍሳችሁን፥ መንፈሳችሁንና ሥጋችሁንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ በንጽሕና ይጠብቅ።

[24] የጠራችሁ እርሱም ይህን ያደርግላችሁ ዘንድ የታመነ ነው።

[25] ወንድሞቻችን ሆይ፥ ጸልዩልን።

[26] በተቀደሰ ሰላምታም ወንድሞቻችንን ሁሉ ሰላም በሉ፤ እርስ በእርሳችሁም ሰላም ተባባሉ።

[27] ይህችን መልእክት ለቅዱሳን ወንድሞቻችን ሁሉ ታነቡአት ዘንድ በጌታችን አምላችኋለሁ።

[28] የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን። ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች የተላከ መጀመሪያይዉ መልእክት ተፈጸመ፤ በአቴና ተጻፈ፤ በጢሞቴዎስና በስልዋኖስ እጅም ተላከ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሜን።

ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 1 — Chapters