[1] መታገሥ ስለ ተሳነንም ብቻችንን በአቴና ልንኖር ወደድን።
[2] በክርስቶስ ወንጌል የሚረዳንን የእግዚአብሔርን አገልጋይ ወንድማችን ጢሞቴዎስን ስለ ሃይማኖታችሁ እንዲያጽናናችሁና እንዲመክራችሁ ላክነው፤
[3] ከእናንተ አንዱ ስንኳ በዚች በመከራችሁ እንዳይናወጥ፥ ተስፋም እንዳይቈርጥ፥ እናንተ ራሳችሁ ይህ ብቻ እንደሚቈየን ታውቃላችሁና።
[4] በእናንተ ዘንድ በነበርንበት ጊዜ መከራ እንደምንቀበልና እንደሚያሠቃዩን፥ አስቀድመን ይህን ብቻ ነገርናችሁ፤ እንደ ነገርናችሁም ያው ሆነ፤ ይህንም ታውቃላችሁ።
[5] ስለዚህም እኔ መታገሥ ተስኖኝ፥ ምናልባት ፈታኝ ፈትኖአችኋል፤ ድካማችንም ለከንቱ ሆኖአል ብዬ ሃይማኖታችሁን አውቅ ዘንድ ጢሞቴዎስን ላክሁት።
[6] አሁን ግን ጢሞቴዎስ ከእናንተ ወደ እኛ ተመልሶ ሃይማኖታችሁንና ፍቅራችሁን፥ በመልካምም ዘወትር እንደምታስቡን፥ እኛ እናንተን ልናያችሁ እንደምንናፍቅ ሁሉ፥ እናንተም ልታዩን እንደምትናፍቁ በነገረን ጊዜ፥
[7] ስለዚህ ወንድሞቻችን ስለ ሃይማኖታችሁ በተቀበልነው በመከራችንና በችግራችን ሁሉ ተጽናናን።
[8] እናንተ በጌታችን ጸንታችሁ ብትቆሙ፥ አሁን እኛ በሕይወት እንኖራለንና።
[9] በእናንተ ምክንያት በአምላካችን ፊት ደስ ስለ አለን ደስታ ሁሉ ስለ እናንተ ለእግዚአብሔር ምን ምስጋና ልናቀርብለት እንችላለን?
[10] ፊታችሁን ለማየት ሌሊትና ቀን አብዝተን እንጸልያለን፤ ሃይማኖታችሁም ፍጹም ይሆን ዘንድ እንለምናለን።
[11] እግዚአብሔር አባታችን፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ወደ እናንተ መንገዳችንን ያቅናልን።
[12] እኛ እናንተን እንደምንወዳችሁ፥ ጌታችን እርስ በርሳችሁ ያላችሁን፥ ከሁሉም ከእያንዳንዱ ጋር የሚሆን ፍቅራችሁን ያብዛላችሁ፤ ይጨምርላችሁም።
[13] ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር በሚመጣበት ጊዜ፥ በአባታችን በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም ልባችሁ በንጽሕናና በቅድስና ይጽና።