[1] “ጵጵስናን ሊሾም የሚወድ መልካም ሥራን ወደደ፤” የሚለው ቃል የታመነ ነው።
[2] ነገር ግን ጵጵስናን የሚሾም እንዲህ ሊሆን ይገባዋል ፥ የማይነቀፍ፥ አንዲት ሴት ያገባ፥ ትጉህ ሰው፥ ብልህ፥ እንደሚገባው የሚሠራ፥ እንግዳ ተቀባይ፥ ራሱን የጠበቀ፥ የሚያስተምርና የሚገሥጽ፥
[3] የማይሰክር፥ ለመማታት እጁን የማያፈጥን፥ ነገር ግን ትዕግሥተኛ፥ የማይጣላና ገንዘብ የማይወድ፥
[4] የቤቱን አስተዳደር በመልካም የሚያስተዳድር፥ በፍጹም ንጽሕና የሚታዘዙ ልጆች ያሉት።
[5] ቤቱን ማስተዳደር የማይችል ሰው የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ያስተዳድራል?
[6] እንዳይታበይና እንዳይነቀፍ፥ በሰይጣን ወጥመድም እንዳይያዝ አዲስ አማኝ አይሁን።
[7] በሰይጣን ነቀፋና ወጥመድ እንዳይወድቅ፥ በውጭ ካሉት ሰዎች መልካም ምስክር ሊኖረው ይገባዋል።
[8] እንዲሁም ዲያቆናት ጭምቶች፥ ቃላቸው የማይለወጥ፥ የወይን ጠጅ መጠጣትን የማያበዙ፥ ከንቱ ትርፍንም የማይወድዱ ይሁኑ፤
[9] የሃይማኖትንም ምሥጢር በንጹሕ ልብ የሚጠብቁ ሊሆኑ ይገባል።
[10] እነርሱንም አስቀድመው ይፈትኑአቸው፤ ከዚህም በኋላ ያለ ነቀፋ ከሆኑ ያገልግሉ።
[11] እንዲሁም ሴቶች ራሳቸውን ያነጹ፥ ሥርዐትን የተማሩ፥ የማያጣሉ፥ ብልሆችና ቅኖች፥ በሁሉም የታመኑ ይሁኑ።
[12] ዲያቆናትም ልጆቻቸውንና የቤታቸውን አስተዳደር በመልካም እየገዙ፥ እያንዳንዳቸው የአንዲት ሴት ባሎች ይሁኑ።
[13] በመልካም ለሚያገለግሉት ከፍተኛውን ሹመት ይስጡአቸው፤ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን ብዙ ባለሟልነት አለና።
[14] ወደ አንተ ፈጥኜ እንደምመጣ ተስፋ አድርጌ ይህን እጽፍልሃለሁ።
[15] የዘገየሁ እንደ ሆነ ግን የእግዚአብሔርን ቤት እንዴት እንደምታስተዳድር ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ የእውነት ዐምድና መሠረት የሕያው እግዚአብሔር ቤት ናት።
[16] የዚህ የመልካም አምልኮ ምሥጢር ታላቅ ነውና። ይኸውም በሥጋ የተገለጠ፥ በመንፈስ የተረዳ፥ ለመላእክት የታየ፥ በአሕዛብ ዘንድ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ በክብር ያረገ ነው።