[1] ሽማግሌዎችን አትንቀፍ፤ ነገር ግን ለእነርሱ እንደ አባትህ፥ ለጐበዞቹም እንደ ወንድሞችህ ታዘዝ።
[2] ለባልቴቶችም እንደ እናትህ ታዘዝ፤ ለወጣቶች ሴቶችም እንደ እኅቶችህ በፍጹም ንጽሕና ታዘዝ።
[3] በእውነት ባልቴቶች የሆኑትን አክብር።
[4] ከእነርሱም መካከል ልጅ ወይም የልጅ ልጆች ያሏት ባልቴት ብትኖር አስቀድሞ ለቤተ ሰዎቻቸው መልካም አምልኮን ያሳዩ ዘንድ፥ ለወላጆቻቸውም ብድራትን ይመልሱላቸው ዘንድ ይማሩ። ይህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና የተወደደ ነውና።
[5] በእውነት ባልቴት የሆነች ብቻዋን የምትኖር ተስፋዋ እግዚአብሔር ነው፤ ሌሊትና ቀንም በጸሎት ተፀምዳ ትኖራለች።
[6] በጨዋታ ተድላ የምታደርግ ግን፥ በሕይወቷ ሳለች የሞተች ናት።
[7] ነውር እንዳይገኝባቸው ይህን ደግሞ እዘዝ።
[8] ለራሱ ስለ ሆኑት፥ ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ፥ ማንም ቢሆን ሃይማኖቱን የካደ ከማያምንም ይልቅ የከፋ ነው።
[9] ባልቴትን ልትሾም ብትመርጥ ዕድሜዋ ስድሳ የሆናትን፥ አንድ ባልም ያገባችውን ምረጥ።
[10] በበጎ ምግባር የተመሰከረላት፥ ልጆችዋን በሥርዐት ካሳደገች፥ እንግዳን ከተቀበለች፥ የጻድቃንን እግር ካጠበች፤ የተራበውን ካበላች፥ በጎ ምግባርንም ሁሉ ከተከተለች ትመረጥ።
[11] ባል የሞተባቸውን ቈነጃጅት ሴቶችን ግን በክርስቶስ ላይ እንዳይቀማጠሉ ራቃቸው፤ አትሹማቸውም፤ እነርሱ ወደ ጋብቻ ሊመለሱ ይወዳሉና።
[12] ፍርድም ይጠብቃቸዋል፤ የቀደመችውን እምነታቸውን ክደዋልና።
[13] ደግሞም መንደር ለመንደር እየዞሩ ሥራ ፈትነትንና ስንፍናን ይማራሉ፤ ሥራ መፍታትን ብቻ አይደለም፤ እንደገና ወሬንና የኀጢአትን ሥራ ሊያራቡ፥ የሌላውን ነገር ይፈጥራሉ እንጂ።
[14] እንግዲህ እኔ ቈነጃጅት እንዲያገቡ፥ ልጆችንም እንዲወልዱ፥ ቤተ ሰዎቻቸውንም እንዲያስተዳድሩ፥ ጠላትም እነርሱን ድል የሚነሣበትን አንዳች ምክንያት እንዳያገኝና ራሳቸውን እንዳያስነቅፉ እፈቅዳለሁ።
[15] ከአሁን በፊት ተመልሰው ሰይጣንን የተከተሉ አሉና።
[16] ከምእመናን ወገን ድሆች ባልቴቶች ያሉት ቢኖር ይርዳቸው፤ ቤተ ክርስቲያንም ረዳት የሌላቸውን እውነተኟች ባልቴቶችን ለመርዳት ትችል ዘንድ ሸክም አይሁኑባት።
[17] በመልካም የሚያስተዳድሩ ቀሳውስት ይልቁንም በመስበክና በማስተማር የሚደክሙ እጥፍ ክብር ይገባቸዋል።
[18] መጽሐፍ ፥ “እህልህን በምታበራይበት ጊዜ በሬውን አፉን አትሰረው፥ ለሚሠራም ደመወዙ ይገባዋል” ይላልና።
[19] ሁለት ወይም ሦስት ምስክሮች ሳይመሰክሩበት በሽማግሌው ላይ ነገር አትስማ፤
[20] ሌላው ደግሞ ይፈራ ዘንድ የተሳሳቱትን በሰው ሁሉ ፊት ገሥጻቸው።
[21] በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ፥ በተመረጡ መላእክቱም ፊት አድልዎ ሳታደርግ ይህን እንድትጠብቅ አዳኝብሃለሁ፤ ከፍርድ በፊትም ሰውን እውነተኛ አታድርገው፤ በአድልዎም ምንም አትሥራ።
[22] በማንም ላይ ፈጥነህ እጆችህን አትጫን፤ በሌሎች ኀጢአትም አትተባበር፤ ራስህንም በንጽሕና ጠብቅ።
[23] ስለ ሆድህ በሽታና ስለ ዘወትር ደዌህ ጥቂት ወይን ጨምር እንጂ ውኃ ብቻ አትጠጣ።
[24] ኀጢአቱ የሚታወቅበት ሰው አለ፤ ወደ ፍርድም ይቀድመዋል፤ ኀጢአቱም የሚከተለው አለ።
[25] እንዲሁም በጎ የሚሠራ ይታወቃል፤ ሥራውም ሌላ የሆነ አይደበቅም።