Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:06

[1] በእግዚአብሔር ፈቃድ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በሚሆን በሕይወት ተስፋ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከጳውሎስ ፥

[2] ለምወድህ ልጄ ለጢሞቴዎስ፥ ከአባታችን ከእግዚአብሔር፥ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስም ጸጋና ምሕረት፥ ሰላምም ለአንተ ይሁን።

[3] ከአባቶቼ ጀምሮ በንጹሕ ልቡና የማመልከውን እርሱን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። ሌሊትና ቀንም በጸሎቴ ዘወትር አስብሃለሁ።

[4] እንባህን አስባለሁ፤ ደስ ይለኝም ዘንድ ላይህ እናፍቃለሁ።

[5] በእናትህ በኤውንቄ፥ በአያትህም በሎይድ ላይ ያደረችውን፤ ጥርጥር የሌለባትን ሃይማኖትህን አስባለሁ፤ በአንተም ላይ ጸንታ እንደምትኖር እተማመናለሁ።

[6] ስለዚህም ምክንያት፥ እጄን በአንተ ላይ በመጫኔ ያገኘኸው የአግዚአብሔር ጸጋ ይታደስልህ ዘንድ አስብሃለሁ።

[7] እግዚአብሔር የኀይልና የንጽሕና፥ የፍቅርና የጥበብ መንፈስን እንጂ የፍርሀት መንፈስን አልሰጠንምና።

[8] እንግዲህስ ለጌታችን ለመመስከር አትፈር፤ እኔንም እስረኛውን አታሳፍረኝ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ኀይል ወንጌልን ለማስተማር መከራን ተቀበል።

[9] ያዳነን፥ በቅዱስ አጠራሩም የጠራን እርሱ ነውና፤ ዓለም ሳይፈጠር በኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰጠን እንደ ፈቃዱና እንደ ጸጋው እንጂ እንደ ሥራችንም አይደለም።

[10] ይህም ሞትን በሻረው፥ ሕይወትንም በገለጣት፥ በወንጌሉም ትምህርት ጥፋትን ባራቀ በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት ዛሬ ተገለጠ።

[11] ለእርሱም እኔ ሐዋርያና ዐዋጅ ነጋሪ፥ ለአሕዛብም መምህር ሆኜ ተሾምሁለት።

[12] ስለ እርሱም መከራ እቀበላለሁ፤ እኔም በእርሱ አምኜ አላፍርም፤ ያመንሁትን አውቃለሁና፤ እስከዚያች ቀን ድረስም አደራ የሰጠሁትን ሊጠብቅልኝ እንደሚችል አምናለሁና።

[13] በኢየሱስ ክርስቶስ ባለ እምነትና ፍቅር፥ ከእኔ ዘንድ የሰማኸው ያ የሕይወት ቃልም ምሳሌ ይሁንልህ።

[14] በእኛ ላይ ባደረው በመንፈስ ቅዱስ መልካሙን አደራህን ጠብቅ።

[15] በእስያ ያሉ ሁሉ እንደ ከዱኝ ይህን ታውቃለህ፤ ከእነርሱም እነ ፊሎጎስና እነ ሄርዋጌኔስ ናቸው።

[16] እግዚአብሔር ለሄኔሴፎሩ ቤት ይቅርታውን ይስጠው፤ ብዙ አሳርፎኛልና፤ በእስራቴም አላፈረምና።

[17] ወደ ሮሜ በደረሰ ጊዜም ፈጥኖ ፈለገኝ፤ ታስሬም አገኘኝ።

[18] በዚያችም ቀን በጌታችን ፊት ይቅርታን እንዲያገኝ እግዚአብሔር ይስጠው። በኤፌሶንም እንዳገለገለኝ አንተ ራስህ መልካም አድርገህ ታውቃለህ።

ወደ ጢሞቴዎስ 2 — Chapters