[1] ልጄ ሆይ፥ አንተም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ በርታ።
[2] በብዙ ምስክሮች ፊት ከእኔ የሰማኸውን ትምህርት ለሌሎች ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች እርሱን አስተምራቸው።
[3] ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሚያገለግል በጎ አርበኛ ሆነህ መከራ ተቀበል።
[4] ወደ ሰልፍ የሚሄድ፥ አለቃውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ነው እንጂ የዚህን ዓለም ኑሮ አያስብምና።
[5] የሚታገልም ቢሆን እንደ ሕጉ ካልታገለ አክሊልን አያገኝም።
[6] የሚደክም አራሽም አስቀድሞ ፍሬውን ሊያገኝ ግድ ነው።
[7] ያልሁህን አስተውል፤ እግዚአብሔርም በሁሉ ነገር ጥበብን ይስጥህ።
[8] በወንጌል እንደምሰብከው፥ ከሙታን ተለይቶ የተነሣውን ከዳዊት ዘር የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስበው።
[9] ስለ እርሱም እንደ ወንጀለኛ እስክታሰር ድረስ መከራ እቀበላለሁ፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም።
[10] ስለዚህ እነርሱ ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን ሕይወትና የዘለዓለም ክብር በሰማያት ያገኙ ዘንድ፥ ስለ ተመረጡት ሰዎች በሁሉ ነገር እታገሣለሁ።
[11] ነገሩ እውነት ነው፤ ከእርሱ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን።
[12] ብንታገሥም ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን፤ ብንክደው ግን እርሱም ይክደናል።
[13] ባናምነውም እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን መካድ አይቻለውምና።
[14] እንግዲህ ይህን አሳስባቸው፤ በቃልም እንዳይጣሉ፥ በእግዚአብሔር ፊት ምከራቸው፤ ይህ ምንም የማይጠቅም፥ የሚሰሙትንም የሚያፈርስ ነውና።
[15] የእግዚአብሔርን ቃል በእውነት አቃንቶ ሲያስተምር እንደማያፍር ሠራተኛ ሆነህ፥ ራስህን የተመረጠ አድርገህ ለእግዚአብሔር ታቀርብ ዘንድ ትጋ።
[16] ነገር ግን ጥቅም የሌለውን የርኩሳንን ነገር ተወው፤ ኀጢአታቸውን ያስፋፉአታልና።
[17] ነገራቸውም በብዙዎች ላይ እንደሚታይና እንደሚሰፋ ቐስል ነው፤ እነርሱም ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ናቸው።
[18] እነዚህም ፥ ከእውነት የወጡና ትንሣኤ ምውታን ፈጽሞ ተደርጎአል የሚሉ፥ የብዙ ሰዎችንም ሃይማኖት የሚለውጡ ናቸው።
[19] “እግዚአብሔር ወገኖቹን ያውቃቸዋል፤ የእግዚአብሔርንም ስም የሚጠራ ሁሉ ከክፉ ነገር ይርቃል።” የሚለው ይህ ማሕተም ያለበት የእግዚአብሔር መሠረት ጸንቶ ይቆማል።
[20] በታላቅ ቤት ውስጥም ከወርቅና ከብር የተሠራ ዕቃ ብቻ አይኖርም፤ ነገር ግን ከዕንጨትና ከሸክላም የተሠራ ዕቃ ይኖራል፤ ለክብር የሚሆን አለ፤ ለውርደትም የሚሆን አለ።
[21] ከዚህም ክፉ ነገር ራሱን ያነጻ ሰው ቢኖር የተቀደሰና ጌታውን ለማገልገል የሚጠቅም፥ ለበጎ ምግባርም ሁሉ የተገባ የክብር ዕቃ ይሆናል።
[22] እንግዲህ ከጕuልምስና ምኟት ራቅ፤ እግዚአብሔርንም በንጹሕ ልብ ከሚጠሩት ሁሉ ጋር ጽድቅን፥ሃይማኖትንም፥ ፍቅርንም፥ ሰላምንም ተከተል።
[23] ጠብን እንደሚያመጣ ዐውቀህ ከሰነፎችና ካልተማሩ ሰዎች ምርመራ ራቅ።
[24] የእግዚአብሔር አገልጋይ ግን አይጣላም፤ ነገር ግን ከሁሉ ጋር እንደ ሕፃን የዋህ፥ ለማስተማር የሚበቃ፥ ክፉ ነገርንም ሁሉ የሚታገሥ ይሆናል።
[25] እውነትን እንዲያውቁ፥ ምናልባት እግዚአብሔር ንስሓን ይሰጣቸው እንደ ሆነ የሚጣሉትን በቅንነት ይመክራል።
[26] ከሰይጣን ወጥመድ እንዲድኑ ፈቃዱን ለመከተል ፈጽሞ አጥምዶአቸዋልና።