Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:23

[1] አሁንም በእግዚአብሔር ፊትና በመንግሥቱ በሚመጣበት ጊዜ፥ በሕያዋንና በሙታን ይፈርድ ዘንድ ባለው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት እመክርሃለሁ።

[2] በዝግታ ቆመህ በጊዜውም ያለጊዜውም ቃሉን ስበክ፤ በሁሉም እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ገሥጽ፤ ዝለፍ፤ ፈጽመህም አጽናና።

[3] ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ጊዜ ይመጣልና፤ ነገር ግን በጆሮአቸው ቀባዛነት እንደ ገዛ ምኟታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያመጣሉ።

[4] እውነትንም ከመስማት ጆሮአቸውን ይመልሳሉ፤ ወደ ተረትም ይመለሳሉ።

[5] አንተ ግን ንቃ፤ በሁሉም ብልህ ሁን፤ መከራ ተቀበል፤ የወንጌላዊ ሥራን ሥራ፤ መልእክትህንም ፈጽም።

[6] እኔ ፈጽሜ ግዳጄን ጨርሻለሁ፤ የማርፍበት ዕድሜዬም ደርሶአል።

[7] መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫዬንም ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖቴንም ጠብቄአለሁ።

[8] እንግዲህስ የጽድቅ አክሊል ይቆየኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው እግዚአብሔር በዚያ ቀን ለእኔ ያስረክባል፤ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም።

[9] በቶሎ ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ ተፋጠን።

[10] ዴማስ ይህን የዛሬውን ዓለም ወድዶ እኔን ተወኝ፤ ወደ ተሰሎንቄም ሄደ፤ ቄርቂስም ወደ ገላትያ፥ ቲቶም ወደ ድልማጥያ ሄደዋል።

[11] ሉቃስ ብቻ ከእኔ ጋር ነው፤ ማርቆስን ከአንተ ጋር አምጣው፤ እርሱ ለመልእክት ይጠቅመኛልና።

[12] ቲኪቆስንም ወደ ኤፌሶን ላክሁት።

[13] ስትመጣም በጢሮአስ በአክርጳ ዘንድ የተውሁትን በርኖሱንና መጻሕፍቱን፥ ይልቁንም ብራናውን አምጣልኝ።

[14] አንጥረኛው እለእስክንድሮስ በብዙ አሠቃየኝ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር እንደ ሥራው ይክፈለው።

[15] አንተም ከእርሱ ተጠበቅ፤ ትምህርታችንን እጅግ ተቃውሞአልና።

[16] በመጀመሪያ ክርክሬ ሁሉም ተዉኝ እንጂ ከእኔ ጋር የተባበረ የለም፤ ይህንም እግዚአብሔር ይቅር ይበላቸው።

[17] የስብከቱ ሥራ በእኔ እንዲፈጸም፥ አሕዛብም ሁሉ እንዲሰሙት፥ እግዚአብሔር ቆመልኝ፤ አጸናኝም፤ ከአንበሳ አፍም ዳንሁ።

[18] እግዚአብሔርም ከክፉ ነገር ሁሉ ያድነኛል፤ ለሰማያዊውም መንግሥት ይጠብቀኛል፤ ለእርሱ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ክብር ይሁን።

[19] ጵርስቅላንና አቂላን፥ የሄኔሴፎሩንም ቤተ ሰብእ ሰላም በል።

[20] አርስጦስ በቆሮንቶስ ቀረ፤ ጥሮፊሞስን ግን ታሞ በመሊጡ ተውሁት።

[21] ከክረምት በፊት እንድትመጣ ፍጠን፤ ኤውግሎስና ጴዴስ፥ ሊኖስም፥ ቀላውድያም ወንድሞቻችንም ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡልሃል።

[22] ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመንፈስህ ጋር ይሁን፤ ጸጋ ከአንተ ጋ ይሁን፤ አሜን። ወደ ጢሞቴዎስ የተላከ ሁለተኛዉ መልእክት ተፈጸመ፤ በሮሜ ተጽፎ፥ በአንክሮሎስ እጅ ተላከ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሜን።

ወደ ጢሞቴዎስ 2 — Chapters