Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 2:53

[1] የእግዚአብሔር ባሪያና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነ ከጳውሎስ፥ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች እምነት፥ እንደ መልካም አምልኮ ያለች እውነትንም በማወቅ፥

[2] ሐሰት የማይናገር እግዚአብሔር ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በሰጠው የዘለዓለም ሕይወት ተስፋ፥

[3] በዘመኑም በመድኀኒታችን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ለእኔ አደራ በተሰጠኝ ስብከት ቃሉን የገለጠ፥

[4] በፍቅርና በሃይማኖት ለምወድድህ ልጄ ለቲቶ፥ ከአባታችን ከእግዚአብሔር፥ ከጌታችንና ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስም ጸጋና ምሕረት፥ ሰላምም ለአንተ ይሁን።

[5] ስለዚህ ምክንያት የቀረውን እንድታደራጅ፥ በየከተማውም እኔ አንተን እንደ አዘዝሁህ ቀሳውስትን እንድትሾም በቀርጤስ ተውሁህ።

[6] የአንዲት ሚስት ባልና የማይነቀፍ፥ የሚያምኑ ልጆችም ያሉት፥ ስለ መዳራት፥ ወይም ስለ አለመታዘዝ የማይከሰስ ማንም ቢኖር ሹመው።

[7] ጳጳስ እንደ እግዚአብሔር መጋቢ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባዋልና፤ የማይኮራ፥ ቐጡ ያይደለ፥ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ፥ ከንቱ ረብን የማይወድ፥

[8] እንግዳ የሚቀበል፥ ምግባሩ መልካም የሆነ፥ ራሱን የጠበቀ፥ ጻድቅ፥ ቅዱስ፥ ራሱን የሚገዛ ይሁን።

[9] ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት ደግሞ ሊመክር፥ ተቃዋሚዎቹንም ሊገሥጽ ይችል ዘንድ፥ እንደ ተማረው በታመነ ቃል ይጽና።

[10] የማይታዘዙ፥ ነገራቸው ከንቱ የሆነ፥ ማስተዋል የጐደላቸውንም የሚያታልሉ፥ ይልቁንም ከአይሁድ ወገን የሚሆኑ ብዙ ናቸውና።

[11] እነዚህ ስለ ነውረኛ ረብ የማይገባውን እያስተማሩ፥ ቤቶችን ሁሉ ስለሚገለብጡ አፋቸውን መዝጋት ይገባል።

[12] የገዛ ራሳቸው ነቢይ የሆነ ከእነርሱ አንዱ ፥ “የቀርጤስ ሰዎች ግብዞች፥ ዘወትር ውሸተኟችና ክፉዎች፥ አውሬዎችና፥ የመሃን ማኅፀን ናቸው፤” ብሎአል። ይህም ምስክርነት በእነርሱ ላይ የታመነ ነው።

[13] ስለዚህም ሃይማኖትን እንዲረዱ በቐርጥ ገሥጻቸው።

[14] የአይሁድን ተረትና እውነትን የሚለውጡ የሰዎችን ትእዛዝ እንዳያመጡ ገሥጻቸው።

[15] ሁሉ ለንጹሓን ንጹሕ ነው፥ ለማያምኑና ለርኩሳን ግን ምንም ንጹሕ የሆነ የለም፤ አእምሮአቸውም፥ ሕሊናቸውም የረከሰ ነውና።

[16] እግዚአብሔርን እንደሚያውቁት በግልጥ ይናገራሉ፤ በሥራቸው ግን ይክዱታል፤ እነርሱም ርኩሳንና የማይታዘዙ፥ በበጎ ሥራም ሁሉ የተናቁ ናቸው።

ወደ ቲቶ። — Chapters