Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 2:25

[1] አንተ ግን ለሕይወት ትምህርት የሚገባውን ተናገር።

[2] ሽማግሌዎችም ከዝሙት የነጹ፥ የነቁና ብልሆች ይሆኑ ዘንድ፥ በሃይማኖት እንዳይጠራጠሩ፥ እንዲፋቀሩና አስተውለው እንዲታገሡ ተናገር።

[3] ባልቴቶችም እንዲሁ በጠባያቸው የተቀደሱ፥ የማያሙና ለመጠጥ የማይገዙ ይሁኑ፤ በጎ የሆነውንም ትምህርት ራሳቸውን ያነጹ ዘንድ ለሴቶች ያስተምሩ።

[4] ወጣቶች ሴቶችንም ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን እንዲወዱ ያስተምሩ፤

[5] በእነርሱ ምክንያት አንድ ሰው እንኳን የእግዚአብሔርን ቃል እንዳይነቅፍ ራሳቸውን የሚገዙ ንጹሖች እንዲሆኑ፥ በጎውን እንዲሠሩ፥ ጠባያቸውንና የቤታቸውን ሥርዐት እንዲያሳምሩ፥ ለባሎቻቸውም እንዲታዘዙ ይምከሩአቸው።

[6] ጎበዞቹንም ሰውነታቸውን እንዲጠብቁ ብልሆችም እንዲሆኑ ምከራቸው።

[7] በበጎ ምግባርም ለሁሉ አርአያና ምሳሌ ሁናቸው።

[8] የሚቃወም ሰው በእኛ ላይ የሚናገረውን መጥፎ ነገር ሲያጣ እንዲያፍር አነጋገርህና ትምህርትህ አንድ ሰው እንኳ በማይንቀው፥ ነውር በሌለበትና ሥርዐት ባለው አነጋገር በንጹሕ ይሁን።

[9] አገልጋዮችም ለጌቶቻቸው ይታዘዙ፤ በሁሉም ደስ ያሰኙአቸው፤ በሁሉም አይጨቃጨቁ።

[10] አይስረቁ፤ ነገር ግን መድኀኒታችን እግዚአብሔር ያስተማረውን ትምህርት በቦታው ሁሉ ያመሰግኑ ዘንድ በንጹሕ ሥራቸው እምነታቸውን ይግለጡ።

[11] የሚያድነው የእግዚአብሔር ጸጋ በሰው ሁሉ ዘንድ ታውቆአልና።

[12] እርስዋም ከኀጢአትና ከዓለም ፍትወት እንለይ ዘንድ፥ በዚህ ዓለምም በጽድቅ፥ በንጽሕናና በፍቅር እንኖር ዘንድ ታስተምረናለች።

[13] የተመሰገነውን ተስፋ የታላቁን የአምላካችንን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥

[14] ከኀጢአት ይቤዠን ዘንድ፥ በበጎ ምግባር የሚፎካከር አዲስ ሕዝብንም ለእርሱ ይመርጥ ዘንድ ስለ እኛ ራሱን አሳልፎ የሰጠ። 2፥9።

[15] ለሁሉ ራስህን ዝቅ እያደረግህ ይህን ለሁሉ ምከርና አስተምር፤ ገሥጽም፤ የሚያስትህም አይኑር።

ወደ ቲቶ። — Chapters