[1] ለገዦችና ለባለሥልጣኖች የሚገዙና የሚታዘዙ፥ ለበጎ ሥራም ሁሉ የተዘጋጁ፥
[2] ማንንም የማይሳደቡ፥ የማይከራከሩ፥ ገሮች፥ ለሰው ሁሉ የዋሃትን ሁሉ የሚያሳዩ እንዲሆኑ አሳስባቸው።
[3] እኛም ደግሞ አስቀድመን የማናስተውል ነበርንና፥ የማንታዘዝ፥ የምንስት፥ ለምኟትና ለልዩ ልዩ ተድላ እንደ ባሪያዎች የምንገዛ፥ በክፋትና በምቀኝነት የምንኖር፥ የተጠላን፥ እርስ በርሳችንም የምንጠላላ ነበርንና።
[4] ነገር ግን የመድኀኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ፥
[5] ዳግም ልደትንና፥ በመንፈስ ቅዱስ መታደስን በሚያሰጥ ጥምቀት በምሕረቱ አዳነን እንጂ በጽድቅ ሥራችን አይደለም።
[6] ይኸውም መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ካሰልን በለጋስነቱ በእኛ ላይ ያሳደረው ነው።
[7] በቸርነቱ እንጸድቅ ዘንድ፥ የዘለዓለምን የሕይወት ተስፋም እንወርስ ዘንድ።
[8] ነገሩ እውነት ነው፤ ስለዚህም እሻለሁ፤ በእግዚአብሔር የሚያምኑ ሰዎች በመልካም ምግባር ሁሉ መረዳዳትን እንዲያስቡ ታጸናቸው ዘንድ እወዳለሁ፤ ሰውንም የሚጠቅመው በጎ ነገር ይህ ነው።
[9] ፈጥረው ከሚናገሩት የጠብና የስንፍና ነገር፥ ከተረትና ከዋዛ ነገር ራቅ፤ ከንቱና የማይጠቅሙ ናቸውና።
[10] ክዶ የሚያስክድን ሰው አንድ ጊዜና ሁለት ጊዜ ከመከርኸውና እንቢ ካለ ተወው።
[11] እንዲህ ያለው ሰው የሚያሳስትና የሚያስክድ መናፍቅ እንደ ሆነ፥ በራሱም ላይ ፍርድን እንደሚያመጣ አስታውቅበት።
[12] አርጢሞንን ወይም ቲኪቆስን ወደ አንተ የላክሁት እንደ ሆነ፥ ፈጥነህ ወደ እኔ ወደ ኒቆጵልዮን ከተማ ና፤ በዚያ ልከርም ቈርጫለሁና።
[13] የሀገሩን ጸሓፊ ዜማስን፥ አጵሎስንም በምንም እንዳይቸገሩ በጕuዞአቸው ተግተህ ርዳቸው።
[14] ወገኖቻችንም ፍሬ ቢሶች እንዳይሆኑ፥ በሚፈለገውም ሥራ ጸንተው እንዲገኙ በጎ ምግባርን ይማሩ።
[15] ከእኔ ጋር ያሉት ሁሉ ሰላም ብለውሃል፤ በሃይማኖት የሚወደንን ሁሉ ሰላም በል፤ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን። ወደ ቲቶ የተላከች መልእክት ተፈጸመች፤ በኒቆጵልዮን ከተማ ተጻፈች፤ በደቀ መዝሙሩ በአርጣማ እጅ ተላከች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሜን።