Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:34

[1] ከኢየሱስ ክርስቶስ እስረኛ ከጳውሎስ፥ ከወንድማችንም ከጢሞቴዎስ፥ በሥራ ለሚተባበረንና ለምንወደው ለፊልሞና፥

[2] ለእኅታችን ለአፍብያ፥ ከእኛም ጋር አብሮ ለሚጋደል ለአክርጳ፥ በቤትህም ላለች ቤተ ክርስቲያን፥

[3] ከአባታችን ከእግዚአብሔር፥ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስም ሰላምና ጸጋ ለእናንተ ይሁን።

[4] ፈጣሪዬን ዘወትር አመሰግነዋለሁ፤ በምጸልየው ጸሎትም ሁልጊዜ አስብሃለሁ።

[5] በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ፥ በቅዱሳንም ሁሉ ዘንድ ያለህን ሃይማኖትህንና ፍቅርህን ሰምቻለሁና።

[6] በኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኘውን መልካሙን ነገር ሁሉ በማወቅ የሃይማኖትህ አንድነት የጸና ይሆን ዘንድ እጸልያለሁ።

[7] ወንድሜ ሆይ፥ የቅዱሳን ሰውነት በአንተ ዘንድ ዐርፋለችና በፍቅርህ ብዙ ደስታንና መጽናናትን አግኝቻለሁ።

[8] ስለዚህም የጽድቅን ትእዛዝ አዝዝህ ዘንድ በክርስቶስ ታላቅ ባለሙአልነት አለኝ።

[9] ይልቁንም እኔ ጳውሎስ ሽማግሌው፥ አሁንም ደግሞ እንደምታውቅ የኢየሱስ ክርስቶስ እስረኛ የሆንሁ ስለ ፍቅር እማልድሃለሁ።

[10] በእስራቴ ስለ ወለድሁት ልጄ ስለ አናሲሞስ እማልድሃለሁ።

[11] አስቀድሞ አልጠቀመህም ነበር፤ ዛሬ ግን ለአንተም ለእኔም እጅግ የሚጠቅም ሆኖአል።

[12] አሁንም ወደ አንተ ልኬዋለሁ፤ ልጄ እንደ መሆኑ ተቀበለው።

[13] በወንጌል ስለ ደረሰብኝም እስራቴ ባንተ ፋንታ ያገለግለኝ ዘንድ በእኔ ዘንድ ላኖረው እፈቅድ ነበር።

[14] ነገር ግን በጎነትህ በፈቃድህ እንጂ በግድ እንዳይሆን አንተ ሳታውቅ ምንም ላደርግ አልወደድሁም።

[15] ለዘለዓለም ይሆንህ ዘንድ ስለዚህ ምናልባት ለጊዜው ተለይቶህ ይሆናል።

[16] ከእንግዲህ ወዲህ እንደ ባሪያ አይደለም፤ ነገር ግን ለእኔ የተለየ የተወደደ ወንድሜ ከሆነ ለአንተማ ይልቅ በሥጋውም፥ በጌታችንም ዘንድ ከባሪያ የሚሻል የተወደደ ወንድም እንዴት አይሆንም?

[17] እንግዲህ አንተ ወንድሜ ከሆንህ እንደ እኔ ተቀበለው።

[18] የበደለህ በደል ቢኖር ግን ወይም የሚከፍልህ ዕዳ ቢኖር፥ በእኔ ላይ ቐጠረው።

[19] እኔ ጳውሎስ ፥ “ስለ እርሱ እከፍላለሁ ” ብዬ በእጄ ጽፌአለሁ። ራስህን እንኳ ልትሰጠኝ ይገባኛል አልልህም።

[20] አዎን፥ ወንድሜ ሆይ፥ በጌታችን ስለ አንተ ደስ ይለኛል፤ እኔንም ደግሞ አሳርፈኝ፤ ሰውነቴንም በክርስቶስ ደስ አሰኛት።

[21] በመታዘዝህ ታምኜ፥ ካዘዝሁህም ይልቅ እንደምትጨምር ዐውቄ፥ ጻፍሁልህ።

[22] ከዚህም ጋር የማርፍበትን ቤት አዘጋጅልኝ፥ በጸሎታችሁ እግዚአብሔር መንገዴን እንደሚያቀናልኝ፥ ከእናንተም ጋር እንደሚያገናኘኝ አምናለሁ።

[23] በኢየሱስ ክርስቶስ ከእኔ ጋር የተማረከ ኤጳፍራስ ሰላም ይልሃል።

[24] በሥራ የምንተባበር ማርቆስ፥ አርስጠሮኮስ፥ ዴማስና ሉቃስም ሰላም ይሉሃል፥

[25] የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን። ወደ ፊልሞና የተላከች መልእክት ተፈጸመች፤ በሮሜ ተጽፋ በአናሲሞስ እጅ ተላከች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሜን።