[1] ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዐይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ።
[2] በኋላ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገው፥ ሁሉንም በፈጠረበት በልጁ ነገረን።
[3] እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የመልኩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በሥልጣኑ ቃል እየደገፈ ኀጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ፥ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ።
[4] በዚህን ያህል መብለጥ ከመላእክት በላይ ሆኖ ከስማቸው የሚበልጥና የሚከብር ስምን ወረሰ።
[5] ከመላእክትስ ከሆነ ጀምሮ ፥ “አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወለድሁህ ” ዳግመኛም ፥ “እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጄ ይሆነኛል ” ያለው ከቶ ለማን ነው?
[6] ዳግመኛም በኵuርን ወደ ዓለም በላከው ጊዜ “የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉ ይሰግዱለታል ” አለ።
[7] ስለ መላእክቱም ፥ “መላእክቱን ነፋሳት፥ የሚላኩትንም የእሳት ነበልባል የሚያደርጋቸው እርሱ ነው ” አለ።
[8] ስለ ልጁ ግን ፥ “ጌታ ሆይ፥ ዙፋንህ ለዘለዓለም ነው፤ የመንግሥትህ በትርም የጽድቅ በትር ነው ” አለ።
[9] “ጽድቅን ወደድህ፤ ዐመፃንም ጠላህ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር አምላክህ እንዳንተ ካሉት ይልቅ የሚበልጥ የደስታ ዘይትን ቀባህ።”
[10] ዳግመኛም እንዲህ አለ ፥ “አቤቱ አንተ አስቀድሞ ምድርን መሠረትህ፤ ሰማያትም የእጆችህ ሥራ ናቸው።
[11] እነርሱ ያልፋሉ፤ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ሁሉ እንደ ልብስ ያረጃል፤
[12] እንደ መጋረጃም ትጠቀልላቸዋለህ፤ ይለወጣሉም፤ አንተ ግን መቼም መች አንተ ነህ፤ ዘመንህም የማይፈጸም ነው።”
[13] ከሆነ ጀምሮ ከመላእክት ፥ “ጠላቶችህን ከእግርህ ጫማ በታች እስከ አደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ ” ማንን አለው?
[14] መላእክት ሁሉ መናፍስት አይደሉምን? የዘለዓለም ሕይወትን ይወርሱ ዘንድ ስለ አላቸው ሰዎችስ ለአገልግሎት ይላኩ የለምን?