[1] ከተናገርነውም ዋናው ነገር ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን።
[2] እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፤ እርስዋም በሰው ሳይሆን በእግዚአብሔር የተተከለች ናት።
[3] ሊቀ ካህናት ሁሉ መባንና መሥዋዕትን ያቀርብ ዘንድ ይሾማል፤ ለዚህም ደግሞ የሚያቀርበው አንዳች ነገር ይኖረው ዘንድ ይገባል።
[4] በምድር ቢሆን ኖሮ፥ ሊቀ ካህናት ባልሆነም ነበር፤ በኦሪት ሕግ መሥዋዕት የሚያቀርቡ ካህናት በእርስዋ አሉና።
[5] እነርሱም ሙሴ ድንኳኒቱን ሲሠራ ሳለ እንደ ተረዳ፥ ለሰማያዊ ነገር ምሳሌና ጥላ የሚሆነውን ያገለግላሉ፤ “በተራራው እንደ ተገለጠልህ ምሳሌ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ተጠንቀቅ ” ብሎት ነበርና።
[6] ዛሬ ግን ኢየሱስ ክርስቶስ የምትበልጠውን አገልግሎት ገንዘብ አደረገ፤ ለታላቂቱ ሥርዐትም መካከለኛ ሆነ፤ የምትበልጠውንም ተስፋ ሠራ።
[7] ፊተኛይቱ ያለ ነቀፋ ብትሆን ኖሮ ሁለተኛይቱን ባልፈለገም ነበር።
[8] ነገር ግን እነርሱን ነቅፎ እንዲህ አለ ፥ “እነሆ፥ ለቤተ እስራኤልና ለቤተ ይሁዳም አዲስ ኪዳን የምሠራበት ዘመን ይመጣል ይላል እግዚአብሔር።
[9] እጃቸውን ይዤ ከምድረ ግብፅ ባወጣኋቸው ጊዜ ለአባቶቻቸው እንደ ገባሁት እንደዚያ ያለ ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልኖሩምና፤ እኔም ቸል ብያቸዋለሁና ” ይላል እግዚአብሔር።
[10] ከእነዚያ ዘመናት በኋላ ለቤተ እስራኤል የምገባው ቃል ይህ ነው ፥ ሕጌን በልባቸው አሳድራለሁ፤ በሕሊናቸውም እጽፈዋለሁ፤ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆኑኛል ይላል እግዚአብሔር።
[11] እንግዲህ አንዱ ሌላውን አያስተምርም፤ ወንድምም ወንድሙን እግዚአብሔርን ዕወቅ ብሎ አያስተምርም፤ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና።
[12] ዐመፃቸውን እምራቸዋለሁና ኀጢአታቸውንም ደግሜ አላስብም።”
[13] አዲስ ትእዛዝ በማለቱ የቀደመችቱን አስረጃት፤ አሮጌና ውራጅ የሆነውስ ለጥፋት የቀረበ ነው።