[1] የሳሌም ንጉሥ፥ የልዑል እግዚአብሔርም ካህን የሆነ፥ ይህ መልከ ጽዴቅ፥ አብርሃም ነገሥታትን ድል ነሥቶ በተመለሰ ጊዜ ከእርሱ ጋር ተገናኝቶ ባረከው።
[2] አብርሃምም ከገንዘቡ ሁሉ ከዐሥር አንድ ሰጠው፤ መጀመሪያ የስሙ ትርጓሜ የጽድቅ ንጉሥ ነበር፤ በኋላም የሳሌም ንጉሥ ተባለ፤ የሰላም ንጉሥ ማለት ነው።
[3] አባት የለውም፤ እናትም የለችውም፤ ትውልዱም አይታወቅም፤ ለዘመኑ መጀመሪያ፥ ለሕይወቱም መጨረሻ የለውም፤ ክህነቱ የወልደ እግዚአብሔር ምሳሌ ሆኖ ለዘለዓለም ይኖራል።
[4] የአባቶች አለቃ አብርሃም ከምርኮው ሁሉ የሚሻለውን ዐሥራት የሰጠውን የዚህን ካህን ክብር ታያላችሁን?
[5] ከሌዊ ልጆችም፥ ክህነትን የሚቀበሉት ከሕዝቡ ማለት ከወንድሞቻቸው፥ እነርሱ ምንም ከአብርሃም ወገብ ቢወጡ ከእነርሱ ዐሥራትን በሕግ እንዲያስወጡ ትእዛዝ አላቸው።
[6] ወገናቸው ላይደለ ለእርሱ ግን አብርሃም ዐሥራትን ሰጠው፤ እርሱም ተስፋ ያለው አብርሃምን ባረከው።
[7] ነገር ግን ታላቁ ታናሹን እንደሚባርከው ያለ ጥርጥር ይታወቃል።
[8] በዚህስ የሚሞት ሰው ዐሥራትን ይቀበላል፤ በወዲያው ግን ሕያው እንደ ሆነ መጽሐፍ የሚመሰክርለት እርሱ ይቀበላል።
[9] እንደ ተነገረም ዐሥራትን የሚቀበል ሌዊ ስንኳን በአብርሃም በኩል ዐሥራትን ሰጠ።
[10] መልከ ጽዴቅ በተገናኘው ጊዜ ገና በአባቱ በአብርሃም ወገብ ነበርና።
[11] እንግዲህ ሕዝቡ በሌዊ ክህነት የተመሠረተን ሕግ ተቀብለዋልና በዚያ ክህነት ፍጹምነት የተገኘ ቢሆን፥ እንደ አሮን ሹመት የማይቈጠር፥ እንደ መልከ ጽዴቅ ሹመት ግን የሆነ ሌላ ካህን ሊነሣ ወደ ፊት ስለምን ያስፈልጋል?
[12] ክህነታቸው ታልፍ ዘንድ አላትና፤ ክህነታቸው ካለፈችም ኦሪታቸው ታልፋለች።
[13] ይህ ነገር የተነገረለት እርሱ በሌላ ወገን ተካፍሎአልና፥ ከዚያም መሠዊያውን ያገለገለ ማንም የለም።
[14] ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደ ወጣ የተገለጠ ነውና፤ ስለዚህም ነገድ ሙሴ ምንም እንኳን ስለ ክህነት አልተናገረም።
[15] ይልቁንም ይህ እጅግ ያስረዳል፤ በመልከ ጽዴቅ ክህነት አምሳል ሌላ ካህን ይነሣል ብሎአልና።
[16] ይኸውም በማያልፍ ሕይወት ኀይል እንጂ ለሥጋና ለደም በተሠራ ሕግ አይደለም።
[17] “እንደ መልከ ጽዴቅ ሹመት የዘለዓለም ካህን አንተ ነህ ” ብሎ ይመሰክራልና።
[18] ስለዚህም የምትደክም፥ የማትጠቅምም ስለ ሆነች የቀደመችው ትእዛዝ ተሽራለች።
[19] ኦሪት ምንም ግዳጅ አልፈጸመችምና፤ ነገር ግን በእርስዋ ፋንታ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት ከእርስዋ የሚሻል ተስፋ ገብቶአል።
[20] እርሱ ያለ መሐላ አልሆነም፤ ያለ መሐላ የተሾሙ ካህናት አሉና።
[21] በመሐላ የሾመውን ግን ፥ “እግዚአብሔር ማለ፥ አይጸጸትምም፤ አንተ እንደ መልከ ጽዴቅ ሹመት የዘለዓለም ካህን ነህ ” አለው።
[22] ኢየሱስ ይህን ያህል በምትበልጥና ከፍ ባለች ሹመት ተሾመ።
[23] ለእነዚያስ ብዙዎች ካህናት ነበሩአቸው፤ ሞት ይሽራቸው፥ እንዲኖሩም አያሰናበታቸውም ነበርና።
[24] እርሱ ግን ለዘለዓለም ይኖራል፤ ክህነቱ አይሻርምና።
[25] ዘወትር በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡትን ሊያድናቸው ይቻለዋል፤ ለዘለዓለምም ሕያው ነውና ያስታርቃቸዋል።
[26] ቅዱስና ያለ ተንኰል፥ ነውርም የሌለበት፥ ከኀጢአተኟችም የተለየ፥ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባናል።
[27] እርሱም እንደ እነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኀጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኀጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።
[28] ኦሪትስ የሚሞት ሰውን ሊቀ ካህናት አድርጋ ትሾማለች፤ ከኦሪት በኋላ የመጣው የእግዚአብሔር የመሐላ ቃሉ ግን ዘለዓለም የማይለወጥ ፍጹም ወልድን ካህን አድርጎ ሾመልን።