Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 4:56

[1] በክርስቶስ እውነት እነግራችኋለሁ፤ ሐሰትም አልናገርም። ሕሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልናል፤

[2] በጊዜው ሁሉ ብዙ ኀዘን፥ የማያቌርጥም ጭንቀት በልቤ አለ።

[3] በሥጋ ዘመዶቼና ወንድሞቼ ስለሚሆኑ እኔ ከክርስቶስ እለይ ዘንድ እጸልያለሁ።

[4] እናህም ልጅነት፥ ክብር፥ ኪዳን፥ ሕግና አምልኮ ያላቸው፥ ተስፋም የተሰጣቸው እስራኤላውያን ናቸው።

[5] እነርሱም አባቶቻችን ናቸው፤ ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ ተወለደ፤ እርሱም ከሁሉ በላይ የሆነ ለዘለዓለም ቡሩክ አምላክ ነው፤ አሜን።

[6] ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል አይታበልም፤ እስራኤል ሁሉ እስራኤላውያን አይደሉምና።

[7] የአብርሃም ዘር ሁሉ ልጆቹ የሆኑት አይደለም፤ ከይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል አለው እንጂ።

[8] ልጆች እንዲሆኑት ተስፋ ያናገረለት የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው፤ እነዚህ ከሥጋ የተወለዱ ግን የእግዚአብሔር ልጆች አይደሉም።

[9] “ከርሞ እንደ ዛሬ ወደ አንተ እመለሳለሁ፤ ሣራም ወንድ ልጅ ታገናለች፤” ብሎ ተስፋ ሰጥቶታልና።

[10] ነገር ግን ለእርስዋ ብቻ አይደለም፤ ርብቃም ለአባታችን ለይስሐቅ መንታ በፀነሰች ጊዜ፥

[11] ሳይወለዱ፥ ክፉና መልካም ሥራም ሳይሠሩ የእግዚአብሔር መምረጡ በምን እንደ ሆነ ይታወቅ ዘንድ፥

[12] እርሱ የጠራው ነው እንጂ ሰው በሥራው የሚመረጥ አንዳይደለም ያውቁ ዘንድ፥ ለርብቃ ፥ “ታላቁ ለታናሹ ይገዛል ” አላት።

[13] “ያዕቆብን ወደድሁ፤ ዔሳውን ግን ጠላሁ ” ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአልና።

[14] እንግዲህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር ያደላልን? አያደላም።

[15] እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው ፥ “የምምረውን እምረዋለሁ፤ ይቅር የምለውንም ይቅር እለዋለሁ።”

[16] አሁንም ለሮጠና ለቀደመ አይደለም፤ እግዚአብሔር ይቅር ላለው ነው እንጂ።

[17] እግዚአብሔርም ለፈርዖን በመጽሐፍ እንዲህ አለው ፥ “ኀይሌን በአንተ ላይ እገልጥ ዘንድ፥ ስሜም በምድር ሁሉ ይሰማ ዘንድ ስለዚህ አስነሣሁህ።”

[18] እነሆ፥ የሚወድደውን ይምረዋል፤ የሚወድደውንም ልቡን ያጸናዋል።

[19] እንግዲህ ምን ትላለህ? አንተ እግዚአብሔርን ትነቅፈዋለህን? ምክሩንስ የሚቃወማት አለን?።

[20] ሰው ሆይ፥ እግዚአብሔርን የምትከራከረው አንተ ምንድን ነህ? ሥራ ሠሪውን እንዲህ አታድርገኝ ሊለው ይችላልን?

[21] ሸክላ ሠሪ ከአንድ ጭቃ ግማሹን ለክብር፥ ግማሹንም ለኀሳር አድርጎ ዕቃን ሊሠራ አይችልምን?

[22] እግዚአብሔርም ኀይሉን የሚገልጽበትን ቅጣቱን ሊያሳይ ቢወድ፥ ትዕግሥቱን ካሳየ በኋላ ለማጥፋት የተዘጋጁትን ቐጣውን የሚገልጽባቸውን መላእክት ያመጣል።

[23] ዳግመናም የክብሩን ባለጠግነት ሊያሳይ ቢወድ አስቀድሞ ለወደዳቸውና ለጠራቸው ለይቅርታ የተዘጋጁ የምሕረት መላእክትን ያመጣል።

[24] ወደ ክብሩ የጠራንና የሰበሰበንም እና ነን፤ ነገር ግን ከአሕዛብም ነው እንጂ ከአይሁድ ብቻ አይደለም።

[25] ነቢዩ ሆሴዕ እንዲህ እንዳለ “ወገኔ ያልነበረውን ወገኔ አደርገዋለሁ፤ ወዳጄ ያልነበረችውንም ወዳጄ አደርጋታለሁ።

[26] የእግዚአብሔር ወገኖች አይደላችሁም ይባሉ በነበሩበት ሀገርም የእግዚአብሔር ልጆች ይሆናሉ።”

[27] ኢሳይያስም ድምፁን ከፍ አድርጎ ስለ እስራኤል እንዲህ አለ ፥ “የእስራኤል ልጆች ቐጥራቸው እንደ ባሕር አሸዋ ቢሆንም የተረፉት ይድናሉ።

[28] እግዚአብሔር በዓለም ውስጥ ያደርገው ዘንድ ያለውን ያለቀና የተቈረጠ ነገርን ይናገራልና።”

[29] ኢሳይያስም አስቀድሞ እንደ ተናገረ “እግዚአብሔር ጸባኦት ዘር ያስቀረልን ባይሆን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆን፥ ገሞራንም በመሰልን ነበር።”

[30] እንግዲህ ምን እንላለን? ጽድቅን ያልፈለጉአት አሕዛብ ስንኳ ጽድቅን አገኙአት፤ በእምነትም ጸደቁ።

[31] እስራኤል ግን ኦሪትን ሲከተሉ መጽደቅ ተሳናቸው፤ የኦሪታቸውን ሥራ አልፈጸሙምና።

[32] ይህስ ስለምን ነው? ጽድቃቸው የኦሪትን ሥራ በመሥራት እንጂ በእምነት ስለ አልሆነ ነው፤ የእንቅፋት ድንጋይ አሰነካከላቸው።

[33] መጽሐፍ እንዲሁ “በጽዮን የእንቅፋት ድንጋይንና የማሰናከያ ዐለትን አኖራለሁ፤ ያመነባትም ለዘለዓለም አያፍርም ” ብሎአልና።

ወደ ሮሜ ሰዎች። — Chapters