[1] ለክንክራኦስ ቤተ ክርስቲያን የምትላላከውን እኅታችንን ፌቤንን አደራ እላችኋለሁ፤
[2] ለቅዱሳንም እንደሚገባ በጌታችን ተቀበሉአት፤ እርስዋ ለብዙዎች፥ ለእኔም ረዳት ናትና፤ ለችግራችሁም በፈቀዳችሁት ቦታ መድቡአት።
[3] በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ከእኔ ጋር የተባበሩትን ጵርስቅላንና አቂላን ሰላም በሉ፤
[4] ስለ እኔ ሰውነታቸውን ለመከራ አሳልፈው ሰጥተዋልና፤ የማመሰግናቸውም እኔ ብቻ አይደለሁም፤ ከአሕዛብ ያመኑ ምእመናን ሁሉ ያመሰግኑአቸዋል እንጂ።
[5] በቤታቸው ያሉትን ማኅበረ ክርስቲያንም ሰላም በሉ፤ ወዳጄ ኤጴኔጦስንም እንዴት ነህ? በሉ፤ ይኸውም በእስያ በክርስቶስ ላመኑ ሁሉ መጀመሪያቸው ነው።
[6] ለእናንተ ብዙ የደከመችላችሁን ማርያምንም ሰላም በሉ።
[7] ከዘመዶቼ ወገን የሚሆኑትን ከእኔ ጋር ያመኑ እንድራናቆስንና ዩልያንን ሰላም በሉ፤ ቀደም ሲል ክርስቶስን እንደ አገለገሉ ሐዋርያት ያውቁአቸዋል።
[8] በክርስቶስ ወንድሜ የሆነውን አምጵልያጦስን ሰላም በሉ።
[9] የክርስቶስን ሥራ በመሥራት የምንተባበረውን ኡሩባኖስን፥ ወዳጄ ስንጣክንንም ሰላም በሉ።
[10] በክርስቶስ የተመረጠውን ኤጤሌንን ሰላም በሉ፤ እነ አርስጠቦሎስንም ሰላም በሉ።
[11] ከዘመዶቼ ወገን የሚሆን ሄሮድዮናን ሰላም በሉ፤ በንርቃሶስ ቤት ያሉትንና በክርስቶስ ያመኑትን ምእመናን ሰላም በሉ።
[12] በጌታችን ስም መከራ የተቀበሉትን የጢሮፊሞናንና የጢሮፊሞስን ወገኖች ሰላም በሉ። በጌታችን ስም ብዙ የደከመች እኅታችንን ጠርሴዳን ሰላም በሉ።
[13] ጌታችን የመረጠው ሩፎንን፥ እናቱንም፥ ለእኔም እናቴ የሆነችውን ሰላም በሉ።
[14] አስቀሪጦስን፥ አልሶንጳን፥ ሄርሜስን፥ ጳጥሮባስን፥ ሄርማስን፥ ከእነርሱ ጋር ያሉ ወንድሞቻችንንም ሰላም በሉ።
[15] ፊሎሎጎስን፥ ዩልያን፥ ኔርዮስን፥ እኅቱንም አሊንጳስን ከእነርሱም ጋር ያሉ ቅዱሳንን ሁሉ ሰላም በሉ።
[16] እርስ በርሳችሁ በተቀደሰ ሰላምታ ሰላም ተባባሉ፤ የክርስቶስ ማኅበረ ክርስቲያንም ሰላም ይሉአችኋል።
[17] ወንድሞቻችን ሆይ፥ እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን፥ መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን እንድታውቁባቸው እማልዳችኋለሁ፤ ከእነርሱም ተለዩ፤
[18] እነርሱ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ያይደለ ለሆዳቸው ይገዛሉና፤ በነገር ማታለልና በማለዛዘብም የብዙዎች የዋሃንን ልብ ያስታሉ፤
[19] መታዘዛችሁም በሁሉ ዘንድ ተሰምቶአል፤ እኔም በእናንተ ደስ ይለናል፤ ለመልካም ነገር ጠቢባን፥ ለክፉ ነገርም የዋሃን እንድትሆኑ እፈልጋለሁ።
[20] የሰላም አምላክም ፈጥኖ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ይቀጥቅጠው፤ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን።
[21] ከእኔ ጋር በሥራ የሚተባበረው ጢሞቴዎስም፥ ከዘመዶቼ ወገን የሚሆኑ ሉቅዮስም፥ ኢያሶንም፥ ሱሲ ጴጥሮስም ሰላም ይሉአችኋል።
[22] ይህችን መልእክት የጻፍኋት እኔ ጤርጥዮስ በጌታችን ስም ሰላም እላችኋለሁ።
[23] እኔንና አብያተ ክርስቲያናትን ሁሉ በእንግድነት የተቀበለ ጋይዮስም ሰላም ብሎአችኋል፤ የከተማው መጋቢ አርስጦስና ወንድማችን ቁአስጥሮስም ሰላም ብለዋችኋል።
[24] ከዓለም አስቀድሞ ምሥጢሩ ተሰውሮ ስለ ነበረ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በማስተምራት ትምህርት ላይ ሊያጸናችሁ የሚችለው እርሱ እግዚአብሔር ነው።
[25] ይህም በነቢያት ቃልና የዘለዓለም ገዥ በሚሆን በእግዚአብሔር ትእዛዝ በዚህ ወራት ተገለጠ፤ አሕዛብ ሁሉ ይህን ሰምተውና ዐውቀው በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ያምኑ ዘንድ።
[26] ብቻውን ጠቢብ ለሆነው ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን፤ አሜን።
[27] የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን። በቆሮንቶስ ተጽፋ ለክንክራኦስ ማኅበረ ክርስቲያን በምትላላከው በፌቤን እጅ ወደ ሮሜ ሰዎች የተላከችው መልእክት ተፈጸመች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን ለዘለዓለሙ አሜን።