Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 3:07

[1] ወንድሞቼ፥ የእኔስ የልቤ ምኟት፥ ወደ እግዚአብሔር የማቀርበው ጸሎትም እስራኤል እንዲድኑ ነው።

[2] ለእግዚአብሔር እንዲቀኑ ምስክራቸው እኔ ነኝና፤ ነገር ግን ዐውቀው አይደለም።

[3] የእግዚአብሔርን ጽድቅ አያውቁአትምና በራሳቸውም ጽድቅ ጸንተው ሊኖሩ ወደዱ፤ ለእግዚአብሔር ጽድቅ ግን መገዛት ተሳናቸው።

[4] የኦሪት ጽድቅ ፍጻሜስ ለሚያምኑበት ሁሉ በክርስቶስ ማመን ነው።

[5] ሙሴም “የኦሪትን ጽድቅ መሥራትን የፈጸመ ሁሉ በእርሱ ይጸድቅበታል ” አለ።

[6] የእምነት ጽድቅ ግን እንዲህ ይላል ፥ “በልብህ ወደ ሰማይ ማን ይወጣል?” አትበል፤ ከሰማይ የወረደው ክርስቶስ ነው።

[7] “ወደ ጥልቁም ማን ይወርዳል?” አትበል፤ ከሙታን ተለይቶ የተነሣው ክርስቶስ ነው።

[8] መጽሐፍ እንዲሁ ፥ “ቃል ለልብህም ለአፍህም ቀርቦልሃል ይል የለምን?” ይህም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው።

[9] ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን ለይቶ እንደ አስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህ።

[10] በልቡ የሚያምን ይጸድቃልና፤ በአፉም የሚመሰክር ይድናልና።

[11] መጽሐፍ ፥ “የሚያምንበት ሁሉ አያፍርም ” ብሎአል።

[12] አይሁዳዊንና አረማዊን አልለየም፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ እግዚአብሔር ባለጸጋ ስለሆነ ለለመነው ሁሉ ይበቃልና።

[13] “የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።”

[14] ነገር ግን ያላመኑበትን እንዴት ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ?

[15] “መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው?” ተብሎ እንደ ተጻፈ ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ?

[16] ነገር ግን ሁሉም የወንጌልን ትምህርት የሰሙ አይደለም፤ ኢሳይያስም ፥ “አቤቱ፥ ምስክርነታችንንስ ማን አመነ? የእግዚአብሔርስ ክንዱ ለማን ተገለጠ?” ብሎአልና።

[17] ማመን ከመስማት ነው፤ መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።

[18] ነገር ግን እንዲህ እላለሁ፤ በውኑ እስራኤል ብቻ አልሰሙምን? መጽሐፍ “ነገራቸው በምድር ሁሉ ተሰማ፤ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ደረሰ ” ብሎ የለምን?

[19] እስራኤል ብቻ አልሰሙምን? ሙሴስ አስቀድሞ እንዲህ ብሎአቸው የለምን? “እኔ በማያስተውሉ ወገኖች አስቀናቸዋለሁ፤ ወገን ባልሆነውም አስቈጣቸዋለሁ።”

[20] ኢሳይያስም ደፍሮ ፥ “ለአልፈለጉኝ ተገኘሁ፤ ለአልጠየቁኝም ተገለጥሁላቸው ” ብሏል።

[21] ለእስራኤል ግን “ሁልጊዜ ከዳተኟችና ወንጀለኟች ወደሆኑት ሕዝብ እጄን ዘረጋሁ ” ብሎአል።

ወደ ሮሜ ሰዎች። — Chapters