[1] እንግዲህ ምን እንላለን? የእግዚአብሔር ጸጋ እንዲበዛ ኀጢአት እንሥራን? አይደለም።
[2] ከኀጢአታችን የተለየን እና እንግዲህ እንዴት ዳግመና በእርስዋ ጸንተን መኖር እንችላለን?
[3] ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቅን እና ሁላችን በሞቱ እንደ ተጠመቅን ሁላችሁ ይህን ዕወቁ።
[4] በሞቱም እንመስለው ዘንድ ከእርሱ ጋር በጥምቀት ተቀበርን፤ እርሱ ክርስቶስ በአባቱ ጌትነት ከሙታን እንደ ተነሣ እናም እንደ እርሱ በሐዲስ ሕይወት እንኖራለን።
[5] በሞቱ ከመሰልነውም በትንሣኤው እንመስለዋለን።
[6] ነገር ግን የኀጢአትን ሥጋ ይሽር ዘንድ ከእርሱ ጋር የተሰቀለው አሮጌው ሰውነታችን እንደ ሆነ ይህን እናውቃለን፤ ከእንግዲህ ወዲያ ዳግመና ለኀጢአት እንገዛ ዘንድ አንመለስም።
[7] የሞተስ ከኀጢአት ነጻ ወጥቶአል።
[8] ከክርስቶስ ጋር ከሞትንም ከእርሱ ጋር በሕይወት እንደምንኖር እናምናለን።
[9] ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ እንደ ተነሣ፥ ዳግመናም እንደማይሞት፥ እንግዲህ ወዲህም ሞት እንደማይገዛው እናውቃለን።
[10] የሞተ አንድ ጊዜ ሞተ፤ በሞቱም ኀጢአትን ሻራት፤ የተነሣም ለእግዚአብሔር ተነሣ።
[11] እንዲሁ እናንተም ራሳችሁን ለኀጢአት ምውታን አድርጉ፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም ለእግዚአብሔር ሕያዋን ሁኑ።
[12] በዚህ በሚሞት ሰውነታችሁ ኀጢአትን አታንግሡአት፤ ለምኟቱም እሽ አትበሉት።
[13] ከሙታን ተለይቶ እንደ ተነሣ፥ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጉ እንጂ ሰውነታችሁን ለኀጢአት የዐመፅ የጦር መሣሪያ አታድርጉት፤ ሰውነታችሁንም ለእግዚአብሔር የጽድቅ የጦር መሣሪያ አድርጉ።
[14] እንግዲህ ኀጢአት አትገዛችሁም፤ የኦሪትን ሕግ ከመሥራት ወጥታችሁ ወደ እግዚአብሔር ጸጋ ገብታችኋልና። ስለ መታዘዝ ምሥጢር
[15] እንግዲህ ምን እንላለን? የኦሪትን ሕግ ከመሥራት ወጥተን ወደ እግዚአብሔር ጸጋ ስለ ገባን ኀጢአት እንሥራን? አይደለም።
[16] ለምትታዘዙለት፥ እሺ ለምትሉትም እናንተ አገልጋዮች እንደ ሆናችሁ አታውቁምን? ለተባበራችሁለትስ ራሳችሁን እንደ አስገዛችሁ አታውቁምን? ኀጢአትንም እሺ ብትሉአት፥ ተባብራችሁም ብትበድሉ እናንት ለሞት ተገዢዎች ትሆናላችሁ፤ ጽድቅንም እሺ ብትሉአት ለበጎ ሥራም ብትተባበሩ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናችሁ።
[17] የኀጢአት ተገዦች ስትሆኑ ምሳሌነቱ ለተሰጣችሁ ለምትማሩት ትምህርት ታዝዛችኋልና እግዚአብሔር ይመስገን።
[18] አሁን ግን ከኀጢአት ነጻ ሁናችሁ ለጽድቅ ተገዝታችኋል።
[19] ስለ ሰውነታችሁ ድካም በሰው ልማድ እነግራችኋለሁ፤ ዕወቁ፤ ቀድሞ ሰውነታችሁን ለኀጢአትና ለርኵuሰት፥ ለዐመፃም እንደ አስገዛችሁ፥ እንዲሁ አሁንም ሰውነታችሁን ለጽድቅና ለቅድስና አስገዙ።
[20] ለኀጢአት ትገዙ በነበረበት ጊዜ ከጽድቅ ነፃ ነበራችሁና።
[21] በዚያን ጊዜ ሥራችሁም እነሆ፥ ዛሬ ታፍሩበታላችሁ፤ መጨረሻው ሞት ነውና።
[22] ዛሬ ግን ከኀጢአት ነጻ ወጣችሁ፤ ራሳችሁንም ለጽድቅ አስገዛችሁ፤ ለቅድስናም ፍሬን አፈራችሁ፤ ፍጻሜው ግን የዘለዓለም ሕይወት ነው።
[23] የኀጢአት ትርፍዋ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር ጸጋ ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የዘለዓለም ሕይወት ነው።