Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 2:57

[1] ወንድሞቻችን፥ ሰውነታችሁን ለእግዚአብሔር ሕያውና ቅዱስ፥ ደስ የሚያሰኝም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እማልዳችኋለሁ። ይህም በዕውቀት የሚሆን አገልግሎታችሁ ነው።

[2] ይህን ዓለም አትምሰሉ፤ ልባችሁንም አድሱ፤ እግዚአብሔር የሚወደውን መልካሙንና እውነቱን፥ ፍጹሙንም መርምሩ።

[3] በተሰጠኝ በእግዚአብሔር ጸጋ ሁላችሁም እንዳትታበዩ እነግራችኋለሁ፤ ራሳችሁን ከዝሙት የምታነጹበትን ዐስቡ እንጂ ትዕቢትን አታስቡ፤ ሁሉም እንደ እምነቱ መጠን እግዚአብሔር እንደ አደለው ይኑር።

[4] በአንዱ ሰውነታችን ብዙ የአካል ክፍሎች እንዳሉ፥ ሥራቸውም ልዩ ልዩ እንደ ሆነ፥

[5] እንዲሁ ሁላችን ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፤ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው አካሎች ነን፤ ስጦታውም ልዩ ልዩ ነው፤

[6] እግዚአብሔርም በሰጠን ጸጋ መጠን ልዩ ልዩ ስጦታ አለን። ትንቢት የሚናገር እንደ እምነቱ መጠን ይናገር።

[7] የሚያገለግልም በማገልገሉ ይትጋ፤ የሚያስተምርም በማስተማሩ ይትጋ፤

[8] የሚመክርም በመምከሩ ይትጋ፤ የሚሰጥም በልግስና ይስጥ፤ የሚገዛም በትጋት ይግዛ፤ የሚመጸውትም በደስታ ይመጽውት።

[9] ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን፤ ከክፉ ራቁ፤ በጎውንም ያዙ፤ ለጽድቅ አድሉ፤

[10] እርስ በርሳችሁ በወንድማማችነት መዋደድ ተዋደዱ፤ የምትራሩም ሁኑ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ፤ መምህሮቻችሁንም አክብሩ።

[11] ለሥራ ከመትጋት አትስነፉ፤ በመንፈስ ሕያዋን ሁኑ፤ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤

[12] በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ ለጸሎት ትጉ።

[13] በችግራቸው ቅዱሳንን ለመርዳት ተባበሩ፤ እንግዳ መቀበልንም አዘውትሩ።

[14] የሚያሳድዱአችሁን መርቁ፤ መርቁ እንጂ አትርገሙ።

[15] ደስ ከሚለው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያለቅሰው ጋርም አልቅሱ።

[16] እርስ በርሳችሁም በአንድ ዐሳብ ተስማሙ፤ ትዕቢትን ግን አታስቡ፤ ራሱን የሚያዋርደውንም ሰው ምሰሉ፤ እና ዐዋቆች ነን አትበሉ።

[17] ክፉ ላደረገባችሁም ክፉ አትመልሱለት፤ በሰው ሁሉ ፊት በጎውን ተነጋገሩ።

[18] ቢቻላችሁስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።

[19] ወንድሞቻችን፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ቐጣን አሳልፏት፥ “እኔ እበቀላለሁ፤ እኔ ብድራትን እከፍላለሁ ይላል እግዚአብሔር ” ተብሎ ተጽፎአልና።

[20] ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማም አጠጣው፤ ይህን ብታደርግ የእሳት ፍሕም በራሱ ላይ ትከምራለህ።

[21] ክፉውን በመልካም ሥራ ድል ንሣው እንጂ ክፉውን በክፉ ድል አትንሣው።

ወደ ሮሜ ሰዎች። — Chapters