Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 4:20

[1] አንተ ሰው ሆይ፥ እውነት ለሚፈርደው ለእግዚአብሔር ምን ትመልስለታለህ? በወንድምህ ላይ የምትጠላውን ያን ሥራ አንተ ራስህ ከሠራኸው በራስህ የምትፈርድ አይደለምን? አንተ ራስህ ያን ሥራ ትሠራዋለህና።

[2] ይህም እንደዚህ በሚያደርጉ ሰዎች ላይ ቅጣት የሚያመጣ የእግዚአብሔር ፍርዱ እውነት እንደ ሆነ እናውቃለን።

[3] አንተ ሰው ሆይ፥ በሌላ ላይ አይተህ የምትጠላውንና የምትነቅፈውን ያን አንተ ራስህ የምትሠራው ከሆነ፥ ከእግዚአብሔር ፍርድ እንደምታመልጥ ታስባለህን?

[4] ወይስ በቸርነቱ ብዛት በመታገሡ፥ ለአንተም እሺ በማለቱ እግዚአብሔርን አላዋቂ ልታደርገው ታስባለህን? የእግዚአብሔርስ ቸርነቱ አንተን ወደ ንስሓ እንዲመልስህ አታውቅምን?

[5] ነገር ግን ልቡናህን እንደ ማጽናትህ፥ ንስሓም እንደ አለመግባትህ መጠን የእግዚአብሔር እውነተና ፍርድ በሚገለጥበት ቀን መቅሠፍትን ለራስህ ታከማቻለህ።

[6] እርሱ በእውነተና ፍርዱ ለሁሉ እንደ ሥራው ይከፍለዋልና።

[7] በበጎ ምግባር ጸንተው ለሚታገሡ፥ ምስጋናና ክብርን፥ የማይጠፋ ሕይወትንም ለሚሹ እርሱ የዘለዓለም ሕይወትን ይሰጣቸዋል።

[8] ለሚክዱና እውነትን ለሚለውጡ፥ ዐመፅንም ለሚወድዱ ሰዎች ዋጋቸው ቐጣና መቅሠፍት ነው።

[9] መከራና ጭንቀት አስቀድሞ በአይሁዳዊ፥ ደግሞም በአረማዊ፥ ሥራዉ ክፉ በሆነ ሰው ሁሉ ላይ ነው።

[10] ምስጋናና ክብር፥ ሰላምም አስቀድሞ ለአይሁዳዊ፥ ደግሞም ለአረማዊ፥ ሥራዉ መልካም ለሆነ ሁሉ ነው።

[11] እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያዳላምና።

[12] ከሕግ ወጥተው የበደሉ በሕግ ይፈረድባቸዋል፤ ያለ ሕግ የበደሉ ሁሉም ያለ ሕግ ይፈረድባቸዋል።

[13] በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚያደርጉ ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙ አይጸድቁምና።

[14] ሕግ የሌላቸው አሕዛብስ እንኳ ለራሳቸው ሕግ ይሠራሉ፤ ራሳቸው ለራሳቸው ሕግን ይደነግጋሉ፤ በሕጋቸው የታዘዘውንም ያደርጋሉ።

[15] በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ፤ ከሥራቸውም የተነሣ ይታወቃል፤ ሕሊናቸውም ይመሰክርባቸዋል፤ ይፈርድባቸዋልም።

[16] ይህም እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ እኔ በወንጌል እንዳስተማርሁ ሰዎችን በልቡናቸው የሰወሩትንና የሸሸጉትን በሚመረምርበት ጊዜ የሚናገሩትና የሚመልሱት እንደሌለ ስለሚያውቁ ነው።

[17] አንተ አይሁዳዊ፥ በኦሪትህ የምታርፍ፥ በእግዚአብሔርም የምትመካ ከሆንህ፥

[18] ፈቃዱን የምታውቅ፥ መልካሙንም የምትለይ፥ ኦሪትንም የተማርህ ከሆንህ፥

[19] አንተ የዕውሮች መሪ፥ በጨለማም ላሉት ብርሃን እንደ ሆንህ በራስህ የምትታመን ከሆንህ፥

[20] ሰነፎችን ልባሞች የምታደርግ፥ ሕፃናትን የምታስተምር፥ ጻድቅና የምትከብርበትን የኦሪትን ሕግ የምታውቅ የምትመስል፥

[21] እንግዲህ ሌላውን የምታስተምር ራስህን እንዴት አታስተምርም? አትስረቁ ትላለህ፤ ነገር ግን አንተ ራስህ ትሰርቃለህ።

[22] አታመንዝሩ ትላለህ፤ ነገር ግን አንተ ራስህ ታመነዝራለህ፤ ወደ ጐልማሳ ሚስትም ትሄዳለህ፤ ጣዖትን ትጸየፋለህ፤ አንተ ግን ቤተ መቅደስን ትዘርፋለህ።

[23] በኦሪት ትመካለህ፤ ነገር ግን አንተ ራስህ ኦሪትን በመሻር እግዚአብሔርን ታቃልለዋለህ።

[24] እንደ ተጻፈም “እነሆ፥ በእናንተ ምክንያት አሕዛብ የእግዚአብሔርን ስም ይሰድባሉ።”

[25] ኦሪትንም ብትፈጽም ግዝረት ትጠቅምሃለች፤ ኦሪትን ባትፈጽም ግን ግዝረትህ አለመገዘር ትሆንብሃለች።

[26] አንተ ሳትገዘር ብትኖር፥ ኦሪትንም ብትጠብቅ አለመገዘርህ መገዘር ትሆንልሃለች።

[27] ተገዝረህ ኦሪትን ከምታፈርስ በተፈጥሮ ያገኘሃት አለመገዘርህ አብራህ ብትኖር ይሻልሃል፤ ኦሪትን ከምታፈርስ ከአንተ ከተገዘርኸው ያ ያልተገዘረው፥ ኦሪትን የሚፈጽመው ይሻላል።

[28] በውኑ ለሰው ይምሰል አይሁዳዊ መሆን ይገባልን? ለሰው ፊትስ ተብሎ ይገዘሩአልን?

[29] ዳሩ ግን አይሁዳዊነት በስውር ነው፤ መገዘርም በመንፈስ የልብ መገዘር እንጂ በኦሪት ሥርዐት አይደለም፤ ምስጋናውም ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከሰው አይደለም።

ወደ ሮሜ ሰዎች። — Chapters