[1] ኢየሱስ መሲሕ እንደ ሆነ የሚያምን ሰው ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል፤ ወላጁንም የሚወድ ሁሉ ከእርሱ የተወለደውን ደግሞ ይወድዳል።
[2] እግዚአብሔርን ብንወድደው፥ ትእዛዙንም ብናደርግ የእግዚአብሔርን ልጅ እንደምንወድደው በዚህ እናውቃለን።
[3] ትእዛዙን እንጠብቅ ዘንድ የእግዚአብሔር ፍቅሩ ይህቺ ናትና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም።
[4] ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ድል ይነሣዋልና፥ ድል መንሣቱም ይህች ናት፤ ዓለምን ድል የሚነሣውም እምነታችሁ ነው።
[5] ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን ድል የሚነሣው ማን ነው?
[6] በውኃና በደም የመጣ ይህ ነው፤ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ፤ በውኃና በደም በመንፈስም እንጂ በውኃ ብቻ አይደለም።
[7] መንፈስም እውነት ነውና የሚመሰክረው መንፈስ ነው።
[8] ምስክር የሚሆኑ ሦስት ናቸውና፤ እነርሱም ፥ መንፈስ፥ ውኃና ደም ናቸው፤ ሦስቱም አንድ ናቸው።
[9] የሰውን ምስክርነት የምንቀበል ከሆነ የእግዚአብሔር ምስክርነት ይበልጣል፤ ስለ ልጁ የመሰከራት የእግዚአብሔር ምስክርነቱ ይህች ናትና።
[10] በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን የእግዚአብሔር ምስክርነት በእርሱ አለ፤ በልጁ የማያምን ግን እርሱን ሐሰተኛ አደረገው፤ እግዚአብሔር ስለ ልጁ በመሰከራት ምስክርነት አያምንምና።
[11] እግዚአብሔርም የዘለዓለምን ሕይወት እንደ ሰጠን፥ ምስክርነቱ ይህቺ ናት። በልጁም ያገኘናት ሕይወት ይህቺ ናት።
[12] ወልድ ከእርሱ ጋር ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ ከእርሱ ጋር የሌለው ግን ሕይወት የለውም።
[13] በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ለእናንተ የዘለዓለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ ይህን ጻፍሁላችሁ።
[14] በእግዚአብሔር ዘንድ ያለችን መወደድ ይህች ናት፤ በስሙ ከእርሱ ዘንድ የምንለምነውን ይሰማናልና።
[15] የምንለምነውንም እንደሚሰማን ካወቅን፥ እንግዲያስ በእርሱ ዘንድ የለመነውን ልመና እንደ ተቀበለን እናውቃለን።
[16] ወንድሙን ለሞት የማያበቃ በደል ሲበድል ያየው ሰው ቢኖር እግዚአብሔርን ይለምንለት፤ ለሞትም የማያበቃ በደል ለበደለው ሰው ሕይወትን ይሰጥለታል፤ ለሞት የሚያበቃ በደል አለና ስለ እርሱ ይለምኑለት ዘንድ የምናገር አይደለሁም።
[17] በደል ሁሉ ኀጢአት ናትና፤ ለሞት የማያበቃ በደልም አለ።
[18] ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ እንደማይበድል እናውቃለን፤ ከእግዚአብሔር የተወለደ ራሱን ይጠብቃል እንጂ ክፉ አያገኘውም።
[19] እኛ ከእግዚአብሔር እንደሆን፥ ዓለም ሁሉ ግን በክፉ እንደ ተያዘ እናውቃለን።
[20] የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እግዚአብሔርን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንኖራለን፤ እርሱም እውነተኛ አምላክና የዘለዓለም ሕይወት ነው።
[21] ልጆቼ ሆይ፥ ጣዖታትን ከማምለክ ራሳችሁን ጠብቁ። መጀመሪያዉ የሐዋርያው የቅዱስ ዮሐንስ መልእክት ተፈጸመ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሜን።