Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 2:12

[1] ከእኔ ከቀሲስ፥ በእውነት ለምወዳቸውና እኔ ብቻ ሳልሆን እውነትን የሚያውቁ ሁሉ ደግሞ ለሚወዱአቸው ለተመረጠች እመቤትና ለልጆችዋ፤

[2] በእኛ ዘንድ ስለ ነበረች፥ አብራን ስላለችው፥ ወደ ፊትም ለዘለዓለም ከእኛ ጋር ስለምትኖረው ስለዚች እውነት።

[3] ጸጋ፥ ምሕረትና ሰላም ከእግዚአብሔር አብ፥ ከእግዚአብሔር አብ ልጅ ከኢየሱስ ክርስቶስም በእውነትና በፍቅር ከእናንተ ጋር ይሁን።

[4] እጅግ ደስ አለኝ፤ ትእዛዙን ከአብ እንደ ተቀበልን ከልጆችሽ በእውነት የሚሄዱ አግኝቼአለሁና።

[5] አሁንም እመቤት ሆይ፤ እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ እለምንሻለሁ፤ ይህች ከመጀመሪያ በእኛ ዘንድ የነበረች ትእዛዝ ናት እንጂ አዲስ ትእዛዝን የምጽፍልሽ አይደለም።

[6] ፍቅራችንም ይህች ናት፤ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ እንሄድ ዘንድ ፍቅራችን ይህቺ ናት፤ ቀድሞ በሰማችኋትም በዚያችው ትሄዱ ዘንድ ትእዛዙ ይህቺ ናት።

[7] ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የማያምኑ ብዙዎች አሳቾች ወደ ዓለም መጥተዋልና፤ ይህም አሳቹ ሐሳዊ መሲሕ ነው።

[8] ፍጹም ዋጋ እንድታገኙ እንጂ የሠራችሁበትን እንዳታጡ ራሳችሁን ዕወቁ።

[9] የሚጠራጠር፥ በክርስቶስም ትምህርት የማይኖር ሁሉ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር የለም፤ በክርስቶስ ትምህርት የሚኖር ግን በአብና በወልድ አለ።

[10] ወደ እናንተ የሚመጣውን፥ ይህንም ትምህርት የማያመጣውን ወደ ቤታችሁ አታስገቡት፤ ሰላምም እንኳ አትበሉት።

[11] ሰላም የሚለው በክፉ ሥራዉ ይተባበረዋልና።

[12] የምጽፍላችሁ ብዙ ነበረኝ፤ ነገር ግን በክርታስና በጥቁር ቀለም ልጽፍላችሁ አልፈቀድሁም፤ ደስታችሁ ፍጹም ይሆን ዘንድ ወደ እናንተ እንደምመጣና ቃል በቃልም እንደማነጋግራችሁ ተስፋ አደርጋለሁና።

[13] የተመረጠችው የእኅትሽ ልጆች ሰላም ይሉሻል፥ ጸጋና ፍቅር ከእናንተ ጋር ይኑር። አሜን። ሁለተኛዪቱ የሐዋርያው የቅዱስ ዮሐንስ መልእክት ተፈጸመች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሜን።