Skip to content
Opens in a new window
Listen to this chapter • 2:25

[1] ከእኔ ከቀሲስ የተላከች መልእክት፥ በእውነት ለምወደው ለወንድማችን ለጋይዮስ ትድረስ፤

[2] ወንድሜ ሆይ፥ መንገድህ ትቃናልህ ዘንድ፥ ሰውነትህንም ደስ በሚያሰኛት ትኖር ዘንድ፥ እኔ ስለ ሁሉ እጸልይልሃለሁ።

[3] ወንድሞቻችን መጥተው አንተ በእውነት እንደምትሄድ ስለ ፍቅርህ በመሰከሩ ጊዜ፥ እጅግ ደስ አለኝ።

[4] ልጆቼ በእውነት ሲሄዱ ከመስማት ይልቅ ከዚች የምትበልጥ ደስታ የለችኝም።

[5] ወንድሜ ሆይ፥ ምንም እንኳ እንግዶች ቢሆኑ፥ ለወንድሞች በምታደርገው ሁሉ የታመነ ሥራ ትሠራለህ።

[6] እነርሱም በቤተ ክርስቲያን ፊት ስለ ፍቅርህ መስክረዋል፤ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ አድርገህ በጕuዞአቸው ብትረዳ መልካም ታደርጋለህ።

[7] ከአሕዛብም አንዳች ሳይቀበሉ ስለ ስሙ ወጥተዋልና፤

[8] ወንድሞቻችን ሆይ፥ እኛም በእውነት የጽድቅ ተሳታፊዎች እንሆን ዘንድ እንደ እነዚህ ያሉትን ልንቀበላቸው ይገባናል።

[9] ለቤተ ክርስቲያን አስቀድሜ ጻፍሁ፤ ነገር ግን በእነርሱ ላይ የበላይ ሊሆን የሚወድ ዲዮጥራጢስ አይቀበለንም።

[10] ስለዚህም እኔ በመጣሁ ጊዜ የሚሠራውን ሥራ አሳስባለሁ፤ በእኛ ላይም የሚናገረው ክፉ ቃል አልበቃው ብሎ ወንድሞቻችንን አንቀበል እስከ ማለት ደርሶአልና፤ ሊቀበሉአቸው የሚወዱትንም ይከለክላቸዋል፤ ዳግመኛም ከቤተ ክርስቲያን ያወጣቸዋል።

[11] ወንድሜ ሆይ፥ በጎ አድራጊ እንጂ ክፉ አድራጊ አትሁን፤ በጎ የሚያደርግ ከእግዚአብሔር ነውና፤ ክፉን የሚያደርግ ግን እግዚአብሔርን አያየውም።

[12] ስለ ድሜጥሮስም ሁሉ ይመሰክሩለታል፤ እውነት ራስዋም ትመሰክርለታለች፤ እኛም መስክረንለታል፤ ምስክርነታችንም እውነት እንደ ሆነች ታውቃላችሁ።

[13] የምጽፍልህ ብዙ ነበረኝ፥ ነገር ግን በጥቁር ቀለምና በብርዕ ልጽፍልህ አልወደድሁም።

[14] ነገር ግን በቶሎ እንደማይህና ቃል በቃል እንደማነጋግርህ ተስፋ አደርጋለሁ።

[15] ሰላም ለአንተ ይሁን፤ ወንድሞቻችንም ሰላም ይሉሃል፤ ወንድሞቻችንንም በየስማቸው ሰላም በል። ሦስተኛዪቱ የሐዋርያው የቅዱስ ዮሐንስ መልእክት ተፈጸመች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሜን።